ከ 2018 ጀምሮ በሚኒሶታ አምስተኛው አውራጃ በአሸናፊነት መንበረ ስልጣንዋን አደላድላ የቆየችው የኮንግረስ አባል ኢልሀን ኦማር በቀጣይ ህዳር ወር በሚደረገው የምርጫ ውድድር ላይ ለሶስተኛ ዙር ለመመረጥ በመዘጋጀት ባለችበት ወቅት ሪፐብሊካውያን ተቀናቃኞችዋ ሮይስ ኋይት እና አብዱራህማን ሹክሪ የኦማርን ሀሳብ የሚስቡ ብርቱ ሙግቶችን ማንሳት ጀምረዋል።
በያዝነው አዲስ አመት መጀመርያ ትውልደ ሱማሌያዊዋ ሹክሪ አብዱራህማን ሪፐብሊካውያኑን ወክላ እንደምትወዳደር ከገለፀች በኋላ የኢልሀን ኦማርን ስህተቶች ነቅሳ በማውጣትዋ ከ ፎክስ ኒውስ ሰፊ ትኩረትን አጊንታለቸ። አሁን ደግሞ በ ሚኒሶታ የተወለደው እና የቀድሞ የ ኤንቢኤ ተጫዋች ሮይስ ኋይት ራሱን ለተመራጭነት እጩ አድርጎ አቅርቧል።
“ለ ኮንግረስ ተመራጭነት የምወዳደረው መሪዎቻችን ስለሸጡን ነው። ለነፃነታችን መታገል አለብን። ማህበረሰባችንን መጠበቅ እና አሜሪካዊ እሴቶቻችንን መመለስ ይገባናል።” ሲል ተናግሯል። ይህንን እሴት ለመመለስም የፖሊስ ለከት አልባ እርምጃዎችን የሚቃወም ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍን ከመምራት ባሻገር ለጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።
እንደ ኢልሀን የፖሊሶች ድጎማ እንዲቀር ባለመጠየቅ እንዲሁም እንደሌሎች የፖሊስ ስርአት አልበኝነትን በዝምታ ባለማለፍ ዋይት መሀከለኛውን መንገድ መርጧል። ፖሊሶች ለጥፋታቸው ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አፅንኦት ከመስጠት ጋር የመኖራቸውን ጥቅምም አልካደም።
በኢልሀን ጉዳይም ቢሆን ከመናገር ወደ ኋላ አላለም። የምርጫ ቅስቀሳዋን በጀመረችበት ወቅት “እርሷ ግሎባሊስት ናት! ይህንን አላማ ለማስፈፀም ተልዕኮዋን እየተወጣች ያለች ተላላኪ ናት። እኔ ደግሞ ለዚህ ማስጠንቀቅያ ለመስጠት ነው የመጣኹት።” ሲል ሸንቆጥ አድርጓታል። ግሎባሊስት ማለት “በሀገር ላይ ኢኮኖሚያዊ ጥቃትን በመፍጠር የአንድን ዜጋ ተፅዕኖ እና ውለታ ማስነስ ነው።” ሲልም ያብራራል።
ዋይት በ 2012 በሆስተን ሮኬትስ ተመርጦ ኤንቢኤን ተቀላቅሏል ይሁን እንጂ ባጋጠመው የአዕምሮ ጭንቀት ዘለግ ላለ ግዜ በ ኤንቢኤ አልቆየም። ለዚህም ይመስላል የዕምሮ ደህንነትን ላይ አትኩሮት ሰቶ የሚሰራው። “የዛሬ አስር አመት በኤንቢኤ ተሳትፌ ነበር። በግዜው የአዕምሮ ደህነነት በቅርቡ የሚገዳደረን ትልቁ ጉዳይ መሆኑን ተናግርያለሁ።” ብሏል።
በ 2012 ኤንቢኤ የተጫዋቾቹ የአዕምሮ ደህንነት ላይ የሚሰራ ምንም አይነት ዝግጅት አልነበረውም። ይህንን የተመለከተው ዋይት ያለምንም ፍራቻ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ፈር ቀዳጅ በመሆን ተናግሯል። ኤንቢኤ ላሳየው ዝንጉነት ከመተቸት ያልተመለሰው ዋይት ካጋጠመው የአዕምሮ ጭንቀት ጋር ተደሞሮ ከ ሮኬትስ አስከትሎም በ 2014 ከኤንቢኤ ለቋል።
የአዕምሮ መታወክ ትኩረት ተሰቶት እየተሰራበት ባለበት ግዜ ዋይት ከራሱ ችግር አልፎ የሌሎችን ችግርር ለመፍታት የባስኬት ቦል ተጫዋችነት ህይወቱን እስከማቆም መወሰኑ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነቱን የሚጨምር ይመስላል። ዋይት “ሌሎች ሀላፊነታችውን ለመወጣት ባልደፈሩበት ግዜ ህልሜን በጭራሽ ተገናኝቻቸው ለማላውቃቸው ሰዎች ለመታገል ስል ትቼዋለሁ።” ብሏል።
ራይት በተከታታይ ሁለት ግዜ ያሸነፈችውን የዴሞክራት ተወካይ ኢልሀን ኦማር ከማሸነፍ በተጨማሪ በሪፐብሊካኑ ወገን እውቅና እየተቸራት ያለችውን ሹክሪ አብዱራህማን ማሸነፍ አለበት። ይህንን መሰናክል አልፎ የሚኒሶታ አምስተኛው አውራጃ ድምፅ በማግኘት የሚያሸንፍ ከሆነ ከ59 አመት በፊት በ ዋልተር ጁድ ተገቶ የቆየውን የሪፐብሊካን የአሸናፊነት ታሪክ ማስመለስ ይችላል።