ሩሲያ በዩክሬን ላይ በወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ዩክሬንን ከማውደሙ ባሻገር በተቀረው አለም ላይ ፍርሀትን ፈጥሯል። ምዕራባውያኑ እና አጋሮቻቸው ዩክሬንን ለማገዝ ሲረባረቡ አፍሪካውያን በ በኩላቸው በጉዳዩ ላይ ተከፋፍለዋል።
የተባበሩት መንግስታት በዩክሬን እና ሩሲያ ውዝግብ ላይ “የሩሲያ የጦር ሀይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከዩክሬን እንዲወጡ!” የሚጠይቅ ድንገተኛ ስብሰባን አድርጓል። በዚህ ድንገተኛ ስብሰባ ላይ 141 አባል ሀገራት ድጋፋቸውን ሲገልፁ፣ 35 ሀገራት ድምፀ ተኣቅቦ በመሆን እና 5 ሀገራት ከዚህ በተቃራኒ መፍትሄውን ነቅፈው መርጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት የጉዳዩን አሳሳቢነት አስመልክቶ መግለጫ ቢያወጣም በአህጉሩ ያሉ አንዳንድ ሀገራት ግን በግልፅ ሩሲያን ከማውገዝ ተቆጠበዋል። ኬንያ፣ ሱማሊያ፣ ጋና እና ናይጄርያ ከ ህብረቱ ጎን ሲቆሙ ሱዳን፣ ዛምቢያ፣ ዚምቧብዌ እና ደቡብ አፍሪካ ጉዳዩን በድምፀ ተአቅቦ አልፈውታል። ኤርትራ በበኩሏ ከሩሲያ ጎን በመቆም ብቸኛዋ አፍሪካዊ ሀገር ሆናለች።
ከሩሲያ፣ ብራዚል፣ ቻይና እና ህንድ ጋር በብሪክስ ቡድን አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ከሩስያ ጋር ዘለግ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያለት ሲሆን በአውሮፓ ህብረት እና በ አሜሪካ አንደኛውን ጎራ በግልፅ እንድትደግፍ ግፊት ቢያድርባትም አንደኛውን ሳታወግዝ ለድርድር ጥሪ አቅርባለች።
ደቡብ አፍሪካውያን ከአፓርታይድ ጋር ያድረጉት በነበረው የነፃነት ትግል ወቅት ሩሲያ ቋሚ ደጋፍያቸው ነበረች። ይህንንም ደቡብ አፍሪካውያኑ የዘነጉ አይመስልም! በቅርቡም በደቡብ አፍሪካ የሩሲያ ኢምባሲ በትዊተር የማህበራዊ ድህረገፅ ትስስሩ ላይ “ውድ ተከታዮቻችን በግልም ሆነ በድርጅት ለሩሲያ አጋርነታቸውን የሚያሳዩ ብዙ ደብዳቤዎች ተቀብለና። ከጎናችን ለመቆም ስለወሰናችሁ ደስተኖች ነን።” ሲል ፅፏል።
ይሁን እንጂ ይህ የደቡብ አፍሪካውያ ድጋፍ እና የደቡብ አፍሪካ መንግስት ጎራ አለመለየት በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት በመልካም አልታየም። በደበቡ አፍሪካ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር የሆነችው ሪና ኪዮንካ በዚህ ተስፋ መቁረጧን አመላክታለች።
በፃፈችው ኢሜልም “መሀል ሰፋሪ መሆን ምርጫ አይደለም። የደቡብ አፊሪካ መንግስት ውግንና ለማን ነው? የሚለውን ካወቅን በኋላ የሚከተለውን ውጤት የምናስብ ይሆናል።” ብላለች።
ኪዮንካ ይህን ትበል እንጂ ደቡብ አፍሪካ መሀል ሰፋሪ ከመሆን ይልቅ ዘለግ ላለ ግዜ የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ሁለተናዊ ግንኙነት ላለማበላሸት ያለመ ነው። “ሩሲያ በየትኛውም ግዜ ጓደኛችን ናት። የነበረንን ግንኙነት ሁሉ ልንክድ አንችልም።” ስትል ትምህርትዋን በሞስኮ የተከታተለችው የደቡብ አፍሪካ ማህበራዊ እድገት ሚኒስተር ሊንዱዌ ዙሉ ተናግራለች።
ከዚህ በተጨማሪ የሱዳን መከላከያ ሀላፊ የሆኑት ሙሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ጦርነቱ በተጀመረበት ቀን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ወደ ሩሲያ አቅንተው ነበር። በ 2020 በተደረገው ስምምነት መሰረት ሱዳን ለሩሲያ የባህር ሀይል መጠቀምያነት ይዞታውን ፈቅዳ ነበር። ይህንንም በማስታወስ መሐመድ ሐምዳን “ሱዳን አሁንም ለሩሲያ የባህር ሀይል በርዋ ክፍት ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጲያውያን በበኩላቸው ጣልያንን ያሸነፉበት የአድዋ ድል ሲያስታውሱ በፍቃደኝነት ለኢትዮጲያ የወገኑ ሩሲያዎችን በማሰብ የሩሲያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ተስተውሏል። በ መከካከለኛው አፍሪካ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎች ለ ሩሲያ በመወገን ሰልፍ የወጡ ሲሆን በሰልፉም ላይ “መካከለኛው አፍሪካ ከሩሲያ ጎን ናት!” የሚል ባነር ይዘው ታይተዋል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት አፍሪካውያ ከሩሲያ ጎን እንዳይቆሙ ግፊት እያደረጉ ቢሆንም የአፍሪካ መንግስታትን እና የአፍሪካውያንን ቀልብ መሳብ የከበዳቸው ይመስላል። በኢትዮጲያ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂ የሆነው ነብዩ ኢልያስ ለሆርን መፅሔት “ምዕራባውያኑ አፍሪካ እና የተቀረውን የአለም ክፍል ይሄን አድርጉ። ይሄን አታድርጉ! የሚለውን ድፍረት ከየት እንዳመጡት ይገርመኛል።” ብሏል።
ለሩሲያ ድጋፋቸውን የሰጡ አፍሪካውያን ቁጥራቸው በርከት ቢልም በግልፅ የሩሲያን ድርጊት ያወገዙም አልጠፉም። ከኬንያ በተጨማሪ ጋና እና ናይጄርያ በግልፅ ሩሲያን በመተቸት ከ አውሮፓ ህብረት ጎን ታይተዋል።