ያለንበት ሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያውን ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት እ.አ.አ በ 2008 አሳይቶናል። ሴቶች የመምረጥ መብታቸውን በ 1920 ካገኙ ከ 95 አመት በኋላ የመጀመርያዋ ሴት የዴሞክራት ፓርቲ እጩ በ2016 ማየት ተችሏል። በተጨማሪም በ2021 የመጀመርያውን ሙስሊም ወደ ፌደራል ፍርድ ቤት ማምጣት ተችሏል። በያዝነው 2022 ደግሞ በ ጆ ባይደን ምርጫ የመጀመርያዋን ሙስሊም ሴት በፌደራል ፍርድቤት የማየት ተስፋ አለ።
የባይደን አንዱ አላማ በወንዶች የበላይነት የተያዘውን የአመራር ቦታ ሁሉን አቀፍ ማድረግ ነው። የሙስሊሙ ማህበረሰብ ቾድሪ እጩ ሆና እንድትቀርብ የዴሞክራት ሴኔት የሆኑት ቻክ ሹመር እና ክሪስቲን ጊልብራንድ ላይ ጫና ፈጥሯል። ይህንን ተከትሎ ባይደን በ 2022 ጥር ላይ እጩ አድርገው ቢመርጥዋትም ሴኔቱ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
በ ኢሊኖይስ የአሜሪካ ሲቪል ሊቤሪቲስ ዩኒየን ዳይሬክተር የሆነችው ኮሌን ኮኔል “ኑስረት ቾድሪ የመጀመርያዋ ባንግላዲሽ አሜሪካዊ ሙስሊም ሴት እና በፌደራል ዳኝነት ሁለተኛዋ ሙስሊም እንደመሆኗ መጠን እጩ መሆንዋ ታሪካዊ ነው።” ብለዋል።
ትውልደ ባንግላዴሺያዊዋ የአሜሪካ ዜጋ ኑስረት ቾድሪ የሲቪል መብቶች ጠበቃ ስትሆን ከ 11 ዓመት በላይ ኒውዮርክ በሚገኘው የአሜሪካ የሲቪል ነፃነቶች ህብረት ላይ ሰርታለች። እንዲሁም በብሄራዊ ደህንነት ፕሮጀክት እና የዘር ተኮር መድሎዎች ላይ ጠበቃ ነበረች። ከ 2020 ጀምሮ ደግሞ በ ኢሊኖይስ የአሜሪካ የሰቪል ነፃነቶች ህብረት የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር በመሆን አገልግላለች።
ቾድሪ በአሁኑ ግዜ በኢሊኖይስ የአሜሪካ ሲቪል ነጻነቶች ህብረት የህግ ዳይሬክተር በመሆን እየሰራች ትገኛለች። በአሜሪካ ሴኔት እጩነቷ የሚጸድቅላት ከሆነ በኒውዮርክ ፌደራል ፍርድ ቤት የምትሰራ ይሆናል።
“የፍትህ ስርዓቱ እኩልነት እየተዛነፈ ባለበት በዚህ ወቅት የሙስሊሙን እና ሌሎች የተገለሉ ማህበረሰቦችን ህዝባዊ መብት ለማስጠበቅ እራስዋን የሰጠችው ቾውድሪ ለፍትህ አካላት ህጋዊነትን እና ተአማኒነትን ታመጣለች።” ሲሉ የሙስሊም ተሟጋቾች ተናግረዋል። አክለውም፦ “ጥላቻ እና መለያየት እኛን እየከፋፈለን ባለበት ጊዜ ቾውድሪ እንደ መጀመሪያዋ ሙስሊም ባንግላዴሺያዊ – አሜሪካዊ ሴት ሙስሊም የፌደራል ዳኛ በመሆን ተምሳሌት ትሆነናለች።” ብለዋል።
ኮኔል ድርጅታቸው በ እጩዎች ላይ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ እንደማይገሰጥ ቢገልጽም ቾውድሪ ግን ለቦታው ከበቂ በላይ ብቁ ናት ብሎ እንደሚያስብ አሳውቋል። “በኢሊኖይስ ውስጥ የህግ ዳይሬክተር ሆና ባገለገለችበት ወቅት ከብዙ በጥቂቱ በቺካጎ የፖሊስ አገልግሎትን ለማሻሻል፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ለወረርሽኙ ተጠቂ በሆነ መልኩ በኢሚግሬሽን ክስ የታሰሩ ሰዎችን ለመጠበቅ እና የቺካጎ ነዋሪዎችን ኪሳራ ውስጥ የሚከቱ ያልተገቡ ክፍያዎችን ለማስቀረት ስትታገል ቆይታለች።” ብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የፌደራል ዳኞችን በእጩነት አቅርበው ሲጨርሱ የዳኞቹ ስያሜ የሚረጋገጠው ግን በሴኔቱ ውሳኔ ነው። ፕሬዘዳንቱ ከ ቾድሪ በተጨማሪ ሰባት እጩዎችን አቅርበዋል። ከእነዚህ መካከል በአሜሪካ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውስጥ የምትሰራው የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት አሪያና ፍሪማን ትገኛለች።
ቾድሪ የፌደራል ዳኛ ሆና የምትመረጥ ከሆነ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሙስሊም ሴት የፌጀራል ዳኝ ስትሆን ከዛሂድ ቁራይሺ በመቀጠል ሁለተኛዋ ሙስሊም የአሜሪካ ፌደራል ዳኛ ትሆናለች።