የተማሪዎች የትምህርት ብድር እዳ ስረዛ ዘለግ ላለ ግዜ አነጋጋሪ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬም ቢሆን ውዝግብ እና ክርክሩ መፍትሄ ሳይበጅለት እየተንከባለለ ይገኛል። እያንዳንዱ አስተዳደር ከንግግር ከፍ ብሎ ሕግ ወደማርቀቅ እየቀረበ በሄደ ቁጥር ባይደን 43 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ አሜሪካውያን በተማሪዎች ብድር ዕዳ ላይ የ 1.7ትሪሊዮን ዶላር የእዳ ስረዛ እንዲያካሄድ ጫና ለመፍጠር ተሞክሯል። ባይደን የተማሪዎችን ብድር ሙሉ ለሙሉ ለመሰረዝ ባያስብም እንኳን ወደ 16 ሚሊዮን ለሚጠጉ የመንግስት ተማሪዎች ብድር ለእይንዳንዱ የ 10,000 ዶላር ምህረት እንደሚያደርግ ይገመታል።
የ እዳ ስረዛው ከመንግስት ኮሌጆች ለተመረቁ ተማሪዎች፣ ቀደም በሉ ግዜያት የጥቁሮች የነበሩ ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች፣ አናሳ ቁጥር ያላቸው የማህበረስብ ክፍሎችን ለሚያገለግሉ ተቋማት እንዲሁም አመታዊ ገቢያቸው ከ 125,000 ዶላር ላነሰ ዜጎች የትምህርት ክፍያ ስረዛንም ጨምሯል።
የ ባይደን እቅድ እስከ 17 ትሪሊዮን የሚጠጋውን የተማሪዎችን እዳ መሰረዝ ሳይሆን ይልቁንም ከፍተኛ መጠን ያለውን እዳቸውን ለመቀነስ ነው። ይህም በ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ባለእዳዎች ገንዘብ ኪሳቸው ላይ ማስቀመጥ እንዲችሉ ያግዛቸዋል። በምላሹ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚያስፈልገውን የወጪ ኃይል ይሰጣቸዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በራሱ ኢኮኖሚውን በማዛባቱ ተማሪዎች ብድራቸውን በራሳቸው ለመክፈል እንዲከብዳቸው አድርጓል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በወረርሽኙ ስራ በማጣታቸው መሰረታዊ ነገሮችን ለማሟላት እየተቸገሩ ይገኛሉ። ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎችም እስካሁን ድረስ የቤት ኪራይ እዳቸውን አጠናቀው መክፈል አልቻሉም። ምን አልባት ይህ ወረርሽኝ ከጠፋ በኋላም ቢሆን አሜሪካውያን ወደ ቀደመ የኢኮኖሚ መረጋጋት ለመመልስ ረጅም አመታት ይፈጅባቸዋል። በዚህ ሁኔታ የትምህርት እዳ ክፈሉ ማለት ተጨማሪ ችግር ውስጥ መክተት ነው።
የምክርቤቱ አባል የሆነችው ኢልሃን ኦማር “የትምህርት እዳ የተሳሳተ ውሳኔ ውጤት ሳይሆን ተማሪዎች የተመቻቸ ህይወት እንዲኖራቸው ትምህርት እንዲማሩ ወይንም የኮሌጅ ዲግሪ እንዲጭኑ እየገፋፋ ይህንን ለማሟሟላት አስፈላጊውን ግብአት ማቅረብ ያቃተው የከሸፈ ስርአት ነው።” ብላለች።
ኢልሃን የአሜሪካን የሁለት እርከን ስርአት ስትቃወም እንዲ ትላለች ሀብታሞች ለተሻለ ትምህርት ገንዘብ የሚያወጡ ሲሆን መካከለኛ እና ዝቅተኛ ህይወት ላይ ያሉት ማህበረሰቦች ግን እድሜያቸውን ሙሉ የትምህርት እዳ እየከፍሉ አንዲኖሩ ይገደዳሉ። ስለዚህ የመጀመሪያው እርምጃ “ለፌዴራል ብድር ተበዳሪዎች እስከ 50 ሺህ ዶላር የተማሪ ዕዳ መሰረዝ ነው” ትላለች። ኢልሃን ከበርኒ ሳንደርስ እና አሌክሳንድሪያ ኦሲሺዮ-ኮርቴዝ ጋር በመሆን ፕሬዝዳንት ባይደን የተማሪ ብድርን ለመሰረዝ የአስፈፃሚ ስልጣናቸውን ይጠቀማሉ የሚል ተስፋ ነበራቸው። ግን ይህን ትልቅ እርምጃ ባይደን እነዲወስድ ለማድረግ ገና ብዙ መንገድ የሚኖር ይሆናል።
ባይደን በበርካታ ዲሞክራት አጋሮቹ 50,000 ዶላር የተማሪ ብድር ዕዳ በአስፈፃሚ ትዕዛዝ አማካይነት እንዲያሰርዝ ተጽዕኖ ቢያደርጉበትም እርሳቸው በበኩላጀው ለዚህ ዝግጁ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር በ 6 ትሪሊዮን ዶላር በጀት ወይም በ ኮቪድ የእርዳታ ዕቅድ ውስጥ የተማሪ ብድር ስረዛን አላካተተም።
ባይደን “ባለው የበጀት እውነታ መሰረት በጣም ብዙ ቁጥር ይሆናል የሚል እምነት የለኝም።” ብለዋል። አስከትለውም “ለፌዴራል የተማሪዎች ከ 5,000 እስከ 10,000 ዶላር ብድር መሰረዝ የምንችል ይመስለኛል።” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ዲሞክራቶች ሴኔቱን እና ምክር ቤቱን የተቆጣጠሩ ቢሆንም የተማሪዎች ብድርን ለመሰረዝ የቀረበውን ረቂቅ ለማፅደቅ አስፈላጊውን ድምፅ ማግኘት አልቻሉም። ይሁን እንጂ ኮንግረስ እስከ ታህሳስ 31/2025 ድረስ የግልም ሆነ የመንግስት ተማሪዎች ብድር ያለ ወለድ እንዲከፈል ግዝያዊ መፍትሄ ሰቷል።
ዴሞክራት አጋሮቻቸው ጆ ባይደን የተማሪዎችን ብድር እንዲሰርዙ እየወተወቷቸው ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ብድሩን በሙሉ ልባቸው ለመሰረዝ ግን አልተስማሙም። ይሁን እንጂ በ ፔል ግራንት ፕሮግራም ስር 85 ቢሊዬን ዶላር በመበጀት የቀኝ ክንፍ ተቀናቃኞቻቸወን ለማባበል በሚመስል መልኩ ድጎማውን በ 1400 ዶላር ከፍ ለማድረግ ወስነዋል።