በዛ ያለ የስራ ፀባይ ዘለግ ላለ ግዜ እንድንቀመጥ በሚያስገድድበት በአሁኑ ዘመን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናማ ህይወትን ለመምራት ወሳኝ ነው። በተለይም በኮቪድ የተነሳ ብዙ ስራዎች ከቤት ውስጥ እንዲሰሩ ከአመት በፊት መወሰኑ ሰዎች በአካል እንቅስቃሴ ላይ ዳተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ቀደም ባሉ ግዜያት የነበሩ ትውልዶች የእለት ተዕለት ስራቸው አካላዊ እንቅስቃሴን የሚፈልግ ስለነበር እንደዛሬው አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረጉ እምብዛም አስፈላጊ አልነበረም።
የአሜሪካ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ማህበር ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ከ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ 61% የሚሆኑ አሜሪካውያን አዋቂዎች አላስፈላጊ የሰውነት ክብደት ጨምረዋል።
በቀኑ ክፍለ ግዜ እንደየስራ ፀባያቸው በተለያየ ወቅት አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ በጠዋቱ ክፍለ ግዜ የሚደረግ አካላዊ እንቅስቃሴ የተሻለ ጥቅም ያለው መሆኑን በዛ ያሉ መረጃዎች በማሳየታቸው ጠዋት አካላዊ እንቅስቃሴ መስራት የሚችሉ ሰዎች ይህን ግዜ ቢጠቀሙት ይመከራል።
በጠዋት የአካል እንቅስቃሴ የማድረግ ጥቅሞች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፦
የክብደት መቀነስ
በጠዋት አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ጠቃሚ ነው። በዚህ ወርቃማ ሰአት ላይ ቁርስ ከመብላት በላይ የሰውነትን ስብ ማቃጠል ቀላል ነው። እንደ ዶክተር አቪታ ሀሪስ ገለፃ ከሆነ በጠዋት በሰውነታችን በዛ ያለ ጉልኮስ የለም ይህም የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። “የለሊቱን ክፍለ ግዜ ስላልበላን እንደ ፆመኛ ነው የምንቆጠረው። ሰውነታችን በዛ ያለ የጉልኮስ መጠን ካለው አካላዊ እንቅስቃሴ ስናደርግ የሚጠቀመው እሱን ነው። ይሁን እንጂ ምግብ ባልወሰድንበት ግዜ እንቅስቃሴው በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ስብ ስለሚጠቀም ከምግብ በፊት የሚደረግ እንቅስቃሴ የሰውነታችንን የስብ መጠን እንዲቀንስ ያደርገዋል።” ሲሉ ዶክተር አቪታ ገልፀዋል።
የተሻለ ትኩረት
በጠዋቱ ግዜ የሚያጋጥመን የስልክ ጥሪ፣ የፅሁፍ መልዕክት ወይንም የ ኢሜል መልዕክቶች አነስተኛ በመሆናቸው በተሻለ ትኩረት እንቅስቃሴያችንን የማድረጋችን እድል ሰፋ ያለ ነው።
የደም ግፊት መቀነስ እና የእንቅልፍ መሻሻል
በ ኬ ፌርብራዘር ተጠንቶ በ ብሔራዊ ባዮቴክኖሎጂ ማህበር ማዕከል የተለቀቀው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእንቅስቃሴው ግዜ በደም ግፊት እና እንቅልፍ ላይ ያለውን ተፅዕኖ የሚያሳየው ጥናት እንዳመላከተው ከሆነ በጠዋት የሚደረግ የ ኤሮቢክስ እንቅስቃሴ የደም ግፊትን ከመቀነስ ባሻገር የእንቅልፍ ጥራትንም ያሻሽላል።
ብሩህ ቀን
ሰዎች ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ስንፍና ተጫጭኗቸው እና የሚያነቃቃቸው ነገር አተው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በጠዋት አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ብሩህ ተስፋ ከመስጠቱ ባሻገር ቀሪውን የቀኑ ክፍለ ግዜ ተነቃቅተው እንዲውሉ ያደርጋል። ዶ/ር አቪታ ሀሪስ “በጠዋት አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ሀይላችን እንዲጨምር እና ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነትም የተሻለ እንዲሆን ያነቃቃናል።” ብለዋል። በጠዋት የሚደረግ አካላዊ እንቅስቃሴ በራስ መተማመናችንን በመጨመር በውስጣችን ያለውን አሉታዊ ሀሳብ ያጠፋል። ይህም በአወንታዊ ሀሳብ የተሞላ ብሩህ ቀን እንድናሳልፍ አስተዋፅኦው ላቅ ያለ ነው።