የሩስያ እና ዩክሬን ግጭት በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዩክሬናዊያን ተፈናቃዮች ላይ ጥፋትን ከማስከተሉ ባሻገር ግጭቱ አለም ላይ በቢሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ አሉታዊ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ተስተውሏል። አፍሪካም ከሌሎች አካባቢዎች በከፋ ሁኔታ ተፅዕኖዎን በምግብ እጥረት እየተጋራች ትገኛለች።
ሩስያ እና ዩክሬን የአለምን አንድ ሶስተኛ የግብርና አቅርቦት ስለሚሸፍኑ የዓለም የምግብ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ በሩሲያ እና ዩክሬን ለም የእርሻ መሬቶች ላይ የተመሰረተ ነው። ለም የእርሻ መሬቱ እንደ ስንዴ እና በቆሎ ያሉ እህሎችን እንዲሁም የሱፍ አበባ ዘይት፣ ማዳበሪያዎች እና የኃይል ምንጮችን ያመርታል። ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ አፍሪካም መሰረታዊ የምግብ ፍላጎቶችን ለማሟላት በእነዚህ ሁለት ምንጮች ላይ ጥገኛ ናት።
ጦርነቱ ገበሬዎች እንዲሰደዱ ከማስገደዱ በተጨማሪ እንደ ቼርኒሂቭ፣ ፖልታቫ፣ ካርኪቭ፣ ሱሚ እና ዢቶሚር የመሳሰሉ የዩክሬን ግብርና የተመሰረተባቸው ቁልፍ ከተሞች እንዲወድሙ ምክንያት ሆኗል። በሀገሪቱ የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ዩክሬን የግብርና ምርቶቿን ወደ ውጭ ከመላክ ተቆጥባለች። ብዙም ሳይቆይ ሩሲያም የግብርና ምርቶችዋን ከሀገር ውስጥ ገበያ ውጪ ወደ ውጪ እንዳይላክ እገዳ ጥላለች።
የዩክሬን የግብርና ሚኒስትር ሮማን ሌሽቼንኮ “በዩክሬን ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል የግብርና ምርትን ወደ ውጭ መላክ መታገድ ይኖርበታል!” ብለዋል። ውሳኔው ገበያውን ለማረጋጋት እና ወሳኝ በሆኑ የምግብ ምርቶች ላይ የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት መሆኑንም ገልፀዋል። እገዳው ማሽላ፣ ቡክኄት፣ ስኳር፣ ከብቶች እና የከብት ተረፈ ምርቶች ወደ ውጭ መላክ ማቆምን ያካትታል።
ጦርነቱ በተጀመረ በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ የ ምግብ ዋጋ 55 በመቶ ጨምሯል። የ ዩክሬን መንግስት የ ህዝቦቹን የምግብ ዋስትና ለመጠበቅ ስንዴ፣ አጃ እና ሌሎች ዋና ዋና ምርቶችን ወደ ውጭ እንዳይላኩ አግዷል። ይህም ከ ዩክሬን ድንበር ውጭ ያሉ ሀገራት እነዚህን መሰረታዊ ፍላጎቶች ከማግኘት ያግዳቸዋል።
በተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የንግድ እና ገበያ ክፍል ኢኮኖሚስት የሆኑት ኤሪክ ኮሊየር “ዩክሬን በብዛት በቆሎ የምትልክላቸው ሀገራት ቻይና እና በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ያሉ ሀገራት ናቸው።” ብለዋል ። አክለውም “እነዚህ ሀገሮች ከዩክሬን ውጪ ካሉ ሌሎች ሀገሮች የምግብ አቅርቦቶችን የማስገባት አቅም አላቸው። ይሁን እንጂ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከዩክሬን ውጭ እህል የማስመጣት አቅም የሌላቸው ሲሆን ዋነኛው የምግብ ምንጫቸውም ከውጪ በሚያስገቡት በቆሎ ላይ የተመሰረተ ነው።” ብላለች።
ባሳለፍነው 2020 አፍሪካ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የግብርና ምርቶችን ከሩስያ አስገብታለች። ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ምርት ስንዴ ሲሆን ከዚህ ላይ 50 በመቶ የሚሆነው ግብጽ የምታስገባው ነው። ከግብጽ ውጪ ሱዳን እና ናይጄሪያ ስንዴን በዋነኝነት ያስገባሉ። ዩክሬን በ 2020 2.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ የግብርና ምርት ለአለም ሀገራት ስትልክ ስንዴ እና በቆሎ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ።
ላለፉት ጥቂት አመታት በኢኮኖሚ ሲችገሩ ለቆዩ ሀገራት የምግብ ዋጋ መናር ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። የደቡብ አፍሪካ የግብርና ቢዝነስ ቻምበር ዋና ኢኮኖሚስት ዋንዲሌ ሺልቦ እንዳሉት “የምግብ ዋጋ እጅጉን ጭማሪ አሳይቷል። ጦርነቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ለርሀብ ሊዳረጉ ይችላሉ። በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሊጠቁ እንደሚችሉ ገምተናል። በሁለቱ ሀገራት መሀከል ያለው ግጭት ደ’ሞ ረሃቡን ያባብሰዋል።” ብለዋል።
በዛ ያሉ ተንታኞች የስንዴ እና የግብርና ምርቶች እጥረት እስከ 2022 መጨረሻ እንደማይታይ ምሁራዊ ትንበያቸውን ቢያስቀምጡም ግብፅ 50% የሚጠጋውን ስንዴ ከውጭ የምታስገባ በመሆኑ የምግብ ዋጋ ንረት ከወዲሁ በ50 በመቶ ጨምሯል።
ጦርነቱ በአፍሪካ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ቢኖረውም አንዳንድ የኢስያ ሀገራትም ስጋት ላይ ወድቀዋል። እንደ ባንግላዲሽ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ኢራን፣ የመን፣ ቱርክ እና ፓኪስታን ያሉ ሀገራት ከሩሲያ እና ዩክሬን በሚመጣ ስንዴ ላይ ጥገኛ ናቸው።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሊባኖስ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ሦስት አራተኛ የሚሆነውን የሀገሯን የስንዴ ፍጆታ ታስገባ ነበር። ነገር ግን ሁለቱም ሀገራት የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ስላቋረጡ የምግብ ዋጋ እየጨመረ መጥቷል። በተጨማሪም በየመን ያለው ግጭትና የዋጋ ንረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሀብ ዳርጓቸዋል። የመን 40% የሚጠጋ ስንዴ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ታስገባለች። ታድያ ይህንን መሰረታዊ የምግብ ምንጭ ማጣት የሚያስከትለው መዘዝ ወደ አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ እንደሚመራ የሚጠብቅ ነው።
የሩስያ እና ዩክሬን ቀውስ በኢኮኖሚ እና በመሠረታዊ የመተዳደሪያ መስፈርቶች ላይ ዓለም አቀፋዊ ተጽእኖ እያሳደረ መምጣቱ ግልጽ ነው። ሆኖም ጦርነቱ በዓለም ዙሪያ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግሮች ከመገመት በዘለለ እስካሁን ምንም አይነት የመፍትሄ ሀሳቦች አልተገኙም። ምን አልባትም ጦርነቱ የሚያመታጣው መዘዝ አለም ከ ሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ያላየችው ነገር ሊሆን ይችላል።