ከአንድ ሚሊየን የሚበልጡ የዩክሬን ዜጎች ሀገራቸውን በመልቀቅ ተሰደዋል። ይህንን ተከትሎ በአለም ላይ ያሉ ሚልየኖች በሀዘኔታ ቢዋጡም የዩክሬን ባለስልጣናት ግን በሀገራቸው ለሚኖሩ አፍሪካውያን የሚገባቸውን ክብር እንክዋ ሊሰጥዋቸው አልወደዱም። ነጭ ስደተኞች በባቡር የሚጓጓዙበት መንገድ ሲመቻች አፍሪካውያን ግን ከዚህ ተገድበዋል።
የተባባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ቁጥር በዚው የሚቀጥል ከሆነ “የክፍለዘመኑ ትልቁ የስደተኞች ችግር” ይሆናል ሲል መግለጫ ሰቷል። የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ የ ስደተኞች ቁጥር በቅርብ ቀናት ወደ 4 ሚሊየን እንደሚያሻቅብ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ለአፍሪካውያን የተነፈገው ከጦር ቀጠና የመውጣት እድል እያለ የተቀረው የአለም ክፍል ለዩክሬናውያን ሀዘኔታውን ለአፍሪካውያን ደግሞ ጥላቻውን እያንፀባረቀ ይቆያል?
ነዋሪነቱን በኻርኪቭ ያደረገው የጊኒ ተወላጅ ሙስጠፋ ባጉ ሲላ በዩክሬን ተማሪ ሲሆን ከሌሎች ዩክሬናውያን ጋር በጋራ ከሀገር ለመውጣት ድንበር ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም እንደ ሌሎች ቀይ የቀለም አይነት እንዳላቸው ሰዎች ግን ያለ ችግር ድንበሩን መሻገር አልቻለም። ድንበር ላይ ጥቁሮች ድንበሩን መሻገር እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል። ሙስጠፋ “ነጮች ግን ድንበሩን ተሻግረው ሲሄዱ ተመልክተናል።” ይላል።
ተመሳሳይ የሆነን ሀሳብ የስፔስ ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነችው የዚምቧቤ ዜግነት ያላት ባርሌ ሙፋሮ ጉሩሬ ተናግራለች። ለአራት ቀናት አሰልቺ የሆነ መንገድን ተጉዛ ድንበር ላይ የደረሰች ቢሆንም ተራዋ ደርሶ ወደ ድንበር ተቆጣጣሪዎቹ ስትቀርብ ግን የድንበር ጠባቂዎቹ እስዋን እና ሌሎች ጥቁር አፍሪካውያንን ገፍተው እንዳባረሯቸው ትናገራለች።
ባርሌ “ከ ኬቭ የወጣነው ነፍሳችንን ለማረፍ ቢሆንም እዚህ እኛን የሚያስተናግዱን ግን እንደ እንስሳ ነው። እንደዚህ ያደርጋሉ ብለን አልጠበቅንም ነበር። ሁላችንም ኩል ነን! እኩል መቆም አለብን። ብዬ ነበር የማስበው!” ትላለች።
የተቀረው የአለም ክፍል ለዩክሬናውያን እርዳታ ከመለገስ ጋር አጋርነቱን እያሳየ ሲሆን የአፍሪካ ሀገራት በበኩላቸው በጥቁር አፍሪካውያን ላይ እየደረሰ ያለውን አድሎ እየተቃወሙ ይገኛሉ። የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ቡኻሪ በትዊተር ገፃቸው “በተባበሩት መንግስታት ህግ መሰረት በጦር ቀጠና ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ በሰላም መንቀሳቀስ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ የከለራቸው ወይም የቆዳቸው ከለር ልዩነት ሊያመጣ አይገባም።” ብለዋል።
አፍሪካ ህብረት በበኩሉ በአፍሪካውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘረኛ ትንኮሳ አስመልኩት መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም “አፍርካውያንን በተለየ መልኩ እየተገለሉበት ያለው መንገድ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ዘረኝነት የተስተዋለበት ከመሆኑም ባሻገር የአለም አቀፍ ህግጋትን የሚፃረር ነው።” ብሏል።
እንደ ሞልዶቭ እና ሮማኒያ ባሉ ጎረቤት ሀገራት የገቡ ጥቁር አፍሪካውያን ልብ የሚያሞቅ ተቀባይነትን ሲያገኙ ፖላንድ በበኩሏ አፍሪካውያን በዩክሬን ግርግዳዎች ተወስነው እንዲቀሩ የበኩልዋን እያደረገች ነው። የዩክሬን ፀጥታ ጠባቂ አፍሪካውያኑን በተለየ መልኩ እያስተናገዱ ያሉት ከፖላንድ በደረሳቸው ትእዛዝ መሆኑን ቢናገርም የ ፖላንድ ሀላፊዎች ግን ጉዳዩን አስተባብለዋል።
ምን አልባት ዜጎች ሀገራቸውን ከወረራ ለመታደግ ከሀገር መውጣት መከልከላቸው ልክ ነው የሚል የመከራከርያ ሀሳብ ይነሳ ይሆናል እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆነም የዩክሬን መንግስት እድሜያቸው ከ 18 እስከ 60 የሆኑ ወንዶች ከሀገር እንዳይወጡ መከልከላቸውን ዘግቧል ይሁን እንጂ አፍሪካውያኑ ዜጋ ባለመሆናቸው በዩክሬን እንዲቆዩ የሚያስገድዳቸው አንዳችም ምክንያት የለም።
አፊሪካዊቷ ክሌር ሙር ባቡር ለመሳፈር ስትወጣ ሴቶች ብቻ ነው የሚሳፈሩት በማለት ጠባቂው እንደገፈተራት ተናግራለች። በግዜው የተሰማትንም “በጣም ደንግጭያለው በዚህ ልክ ዘረኛነቱ የጠና ይሆናል ብዬ አልጠበኩም ነበር።” ብላለች። ሌላ አፍሪካዊ በበኩሏ ባቡር ልትሳፈር ስትል “ቅድሚያ ለእኛ ሴቶች!” እንደተባለች በግርምት ተናግራለች።
ለዚህ ቅጥ ያጣ አድሎ መንስኤው የጥቁሮች ህይወት ከነጮች ያነሰ ቦታ ነው ያለው የሚል ነው። ይህንንም ሀሳብም የሚዲያ ዘጋቢዎች ሲያስተጋቡት ተስተውለዋል። አንድ ዘጋቢ “ሰማያዊ አይን እና ፈዛዛ ቢጫ ፀጉር ያላቸው አውሮፓውያን ሲሞቱ ሞተው ማየት ስሜት ይነካል።” ሲል ሌላ ዘጋቢ “ይህ በማደግ ላይ ያለ የሶስተኛው አለም አይደለም። ይህ አውሮፓ ነው!” ሲል ተሰምቷል። የሰዎች ህይወት በአይናቸው ከለር እና በሚኖሩበት ቦታ መተመኑ የሚያሳዝን ነው!