ሰኞ ጠዋት ጥቅምት 29 ቀን 2018 ከ ጃካርታ አየር ማረፍያ የተነሳው ቦይንግ 737 ማክስ በውስጡ የነበሩትን 189 ተሳፋሪዎች ይዞ የተከሰከሰው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነበር። ይህ የቦይንግ ምርት ለሆነው የማክስ አውሮፕላን የመጀመርያ ትልቅ አደጋ ነው። የዚህ አደጋ አነጋጋሪነት ሳይደበዝዝ ከ አምስት ወር በኋላ ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት የተነሳው ቦይንግ ማክስ አውሮፕላን ከ ስድስት ደቂቃዎች በኋላ ተከስክሶ በድጋሚ የአለምን ህዝብ አስደንግጧል።
በ መጋቢት 10/2019 በኢትዮጲያ ከአዲስ አበባ 65 ኪሜ ርቀት ላይ የተከስከሰው ቦይንግ ማክስ በውስጡ የነበሩትን 157 ተሳፋሪዎች በሙሉ ህይወታቸውን ሲነጥቅ የሟች ቤተሰቦችን በሀዘን ውስጥ ከቶ ደንበኞቹ ጥያቄ እንዲሰነዝሩበት እና ድርጅቱ ለአደጋው መንስኤ ማብራሪያ እንዲሰጥ አሳስቦ ያለፈ ነበር።
የፌደራል አቬሽን አስተዳደር እንዳሳወቀው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በተከታታይ የተከሰቱት ሁለቱ አድጋዎች መካከል ግንኙነት እንዳለ እና አብራሪዎች አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር እንዳይችሉ አውሮፕላኑ ላይ ያለው የመቆጣጠርያ ስርአት እንዳገዳቸው ተገልፅዋል። ከሁለተኛው አደጋ በኋላ ቦይንግ ማክስን ከማብረር ታግዷል! በተጨማሪም የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በይፋ የቦንግን ማክስ 737 አውሮፕላኖችን ከበረራ የሚያግድ አዋጅ ከማውጣት አልፎ ክስ መስርቶበታል። ቦይንግ የቀረቡበትን ክሶች፣ የፌደራል ተቆጣጣሪዎችን እንዲሁም በአክሲዎን ገበያው ላይ የደረሰበትን የዋጋ መሽቆልቆል እየተጋፈጠ መፍትሄዎችን እየፈለገ የ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ለ 20 ወራት ያህል ከሰማይ ላይ አርቆ ቆይቷል።
ከነዚያ የማይሽሩ ሁለት አደጋዎች አስከትሎ ለ ሁለት አመት ገደማ የበረራ ክልከላ ተደርጎበት የቆየው ቦይንግ በድጋሚወደ ስራ ተመልሷል። በአዲሱ ማክስ ሞዴል ላይ የ ሶፍትዌር፣ የኤሌክትሪክ ሲስተም፣ የአሰራር መመሪያዎች እና የሰራተኞች ስልጠናን ጨምሮ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቦይንግ አውሮፕላኖቹ ባደረሱት አደጋ ለተጎዱ ለእያንዳንዱ ተጎጂ ቤተሰቦች 1.4 ሚሊየን ዶላር መድቧል። እነዚህ የማሻሻያ ስራዎች የአውሮፓ አቪዬሽን ባለስልጣን መስፈርቶችን በማሟላት ቦይንግ በድጋሚ የበረራ ፍቃድን እንዲያገኝ በቂ ነበሩ። የአውሮፓ ህብረት የአቪዬሽን ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፓትሪክ ኪይ “የአውሮፓ ህብረት አቪዬሽን ደህንነት ኤጀንሲ ሰፊ ክትትል እና ምርመራ በማድረግ ማክስ 737 ወደ አገልግሎት መመለስ እንደሚችል ወስነናል።” ብለዋል።
በዚህ ብቻ ቦይንግ ከዚህ ቀደም ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች አስተካክሏል ማለት እንችላለን?! በፍፁም። ቦይንግ ባለፉት አመታት ያጣውን የህዝብ አመኔታ በዚህ ፍጥነት በድጋሚ ያገኛል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይደለም። ደምበኞች ቦይንግን የሰለቹት ይመስላሉ፣ ባለ አክሲዎኖች የማክስ ወደ ገበያ መመለስ እና ወደ ቀድሞ የከፍታ ዘመኑ መመለሱ ላይ ሙሉ እመነት አላቸው ማለት ያዳግታል። በኢትዮጵያ ካጋጠመው አደጋ በፊት በ 2019 መጀመርያ የቦይንግ ስቶክ ዋጋ 450 ዶላር ነበር ይሁን እንጂ ከአደጋው በኋላ በዛው አመት አጋማሽ ላይ ዋጋው አሽቆልቁሎ 300 ዶላር ሲገባ በዚው ውድቀቱ ቀጥሎ በ 2020 መጀመሪያ 300 የነበረው የአክሲዮን ዋጋ በግማሽ ቀንሶ 150 ዶላር ገብቷል።
ማክስ ወደ ገበያ በመመለሱ እና የአክሲዎን ዋጋ በ2020 መጨረሻ እና በ2021 መጀመሪያ ወደ 200 ዶላር ከፍ በማለቱ ቦይንግ እንደ አዲስ እያንሰራራ ነው። የ አሜሪካ አየር መንገድ 34 ማክስ አውሮፕላኖችን ያዘዘ ሲሆን 6 አሮፕላኖችን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በ ታህሳስ 29 ቀን 2020 የመጀመሪያ በረራውን ከ ሚያሚ ወደ ኒውዮርክ ካደረገ በኋላ አየር መንገዱ ደንበኞቹን እንደ ሌሎች ሞዴሎች ሁሉ በ ማክስ ላይም በረራ እንደሚያካሂድ ተናግሮ ነበር። በዚህም አክሲዎኑ በዝግታ በማደግ ላይ እያለ እና የተለያዩ አየር መንገዶችምን ደንበኞቻቸውን በ ማክስ ላይ መሳፈር ከጀመሩ በኋላ ቦይንግ መቋቋም የማይችለው ከባድ አደጋ ተጋፍጦበታል። ይህም የድርጅቱ ምርት የሆነው ቦይንግ 737-500 አውሮፕላን የካቲት 10 ቀን 2020 በኢንዶኔዢያ ለ ሁለተኛ ግዜ መከስከሱ ነበር።
ይህ በኢንዶኔዢያ ውስት የተከሰተው የቅርብ ግዜ አደጋ 62 ተሳፋሪዎችን ይዞ ከተነሳ ከ4 ደቂቃዎች በኋላ ከ ጃካርታ ወደ ፖንቲያግ ሲጓዝ ወደ ጃቫ ባሕር ውስጥ በመግባቱ አንድም በሂወት የተረፈ ተሳፋሪ አልነበረም። የዚህኛው አደጋ መንስኤ ከቀዳሚዎቹ ሁለት አደጋዎች ጋር አይያያዝም፡፡ ይህ በቅርብ ግዜ የተከሰከሰው አውሮፕላን ከ ቦይንግ ማክስ 737 በእድሜ የቀደመ ሞዴል ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ምርመራዎች እንዳመላከቱት ለ ሁለቱ የቀድሞ ማክስ 737 አደጋዎች ሞተሮች ላይ የተፈጠረው ሚዛናዊ ያልሆነ የግፊት መጠን ለአደጋው መፈጠር ዋነኛ ነበረው። በአደጋዎቹ ከተሳፋሪዎች መሀከል አንድም የተረፈ አልነበረም። ይህም ለተጎጂ ቤተሰቦች በቀላሉ የሚሻር አይደለም።
የተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ሀዘን ላይ ናቸው! ከፊሎቹ ቦይንግ በበቂ ሁኔታ ለጥፋቱ እንዳልተቀጣ በማሰባቸው በሚያዩት ነገር ደስተኛ አይደሉም። በኢትዮጲያ በተከሰተው አደጋ ባለቤቷን ያጣችው ብሪትኒ ሪፌል ማክስ የበረራ ፈቃድ ለማገኘት እንደፈጠነ ትናገራለች። “ቦይንግ እና የ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር የደህንነት ባህላቸው ከሰው ልጅ ደህንነት ይልቅ ትርፍን እንደሚያስቀድሙ ለሁሉም በመናገር ድምፃችንን እያሰማን ነው!” ብላለች። በአደጋው ባለቤቱን ፣ ሦስት ልጆቹን በተጨማሪም የባለቤቱን እናት ያጣው ፖል ነጆሮጌ “ቤተሰቦቼ የሞቱት በቦይንግ ቸልተኝነት፣ እብሪተኝነት፣ የአመራር ብልሹነት እንዲሁም የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር የውስጥ ቁጥጥር እጥረት ምክንያት ነው።” ብሏል።
ቦይንግ ከ መቶ በላይ ክሶች ያጋጠሙት ሲሆን በተከታታይ አመታት መቶ ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ቃል ገብቷል። የፍትህ መምሪያ ቢሮ እንዳሳወቀው ቦይንግ ለወንጀል ቅጣት፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች እና በአውሮፕላኑ እገዳ ምክንያት መብረር ላልቻሉ ደንበኞች በአጠቃላይ 2.5 ቢሊየን ዶላር ለመክፈል መስማማቱን አስታውቋል፡፡