የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የተማሪዎች ብድር ክፍያ ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር። ይህንን እገዳ ለማንሳትም ላለፉት ሁለት አመታት ንግግሮች እየተደረጉ የነበረ ቢሆን የኮቪድ ዳግመኛ ማንሰራራት ንግግሮቹን በአጭሩ ቋጭቷቸዋል። በስተመጨረሻም የብድር ክፍያው የሚጀምርበት ጊዜ ከግንቦት 2022 እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ተራዝሟል።
የተማሪ ብድር ክፍያን ማቋረጥ በኮሮና ቫይረስ እርዳታ እና የኢኮኖሚ ደህንነት ህግ ውስጥ የሚካተት ሲሆን የ “ኬር” ህግ በመባል ይታወቃል። ህጉ በመጋቢት 2020 በፕሬዚዳንት ትራምፕ ሲጸድቅ የ2.2 ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ድጎማን ይጨምራል።
ሚያዝያ 6 ላይ የአሜሪካ የትምህርት ክፍል የተማሪ ብድር ክፍያ መቋረጥ ከግንቦት 1 እስከ ነሐሴ 31 ድረስ መራዘሙን ሪፖርት አድርጓል። ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው የፌደራል ተማሪ ተበዳሪዎች ከክፍያ ነፃ ናቸው። ነገር ግን ለመጀመርያ ጊዜ ከተራዘመበት ቀን አንስቶ አሁን በቅርቡ አዲስ ማራዘሚያ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ለበርካታ ጊዜያት ሲራዘም ቆይቷል።
ትራምፕ ህጉን ካጸደቀ በኋላ የተማሪዎች ብድር ክፍያ ላይ የተደረገው እገዳ መስከረም 30/2020 ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዶ ነበር። ነገር ግን እስከ ታህሳስ 31/2020 ከዚያም እስከ ጥር 31/2021 ድረስ ሁለት ጊዜ ተራዝሟል። ባይደን ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላም እንዲሁ ተጨማሪ ማራዘምያዎችን አድርጓል።
“በጥር 2021 በመጀመርያ የስራ ቀኔ የተማሪዎች ብድር ክፍያን መቆምን በያዝነው አመት እስከ መስከረም ድረስ እንዲተላለፍ ለፌደራል የትምህርት ክፍል መመሪያ ሰጥቻለሁ” ብሏል። የአሜሪካ ተጠባባቂ የትምህርት ዘርፍ ፀሐፊ ፊል ሮዘንፌልት እስከ መስከረም 2021 ድረስ ያለውን ቆይታ አራዝመዋል። ነገር ግን የተሰጠው ማራዘሚያ ወደ ማብቂያው በመጣ ቁጥር አዲስ ማራዘሚያ ይሰጥ ነበር።
በግዜው ይህ የማራዘምያ ግዜ የመጨረሻው እንደሚሆን አስተዳደሩ ማረጋገጫ የሰጠ ቢሆን በ ነሐሴ 2021 የትምህርት ክፍሉ የብድር ክፍያ የእረፍት ጊዜው እስከ ግንቦት ድረስ እንደሚራዘም አስታውቋል። አሁን ደግሞ እስከ ነሐሴ ድረስ ሌላ ያልተጠበቀ ማራዘሚያ ተደርጓል።
“አሁንም ከወረርሽኙ እና ወረርሽኙ ከፈጠረው ከዚህ በፊት ታይቶ ከማይታወቅ የኢኮኖሚ ችግር እያገገምን ነው።” ብለዋል ባይደን። የተማሪ ብድር ክፍያ መራዘሙ “ተበዳሪዎች የላቀ የፋይናንስ ዋስትና እንዲያገኙ ለመርዳት እና የትምህርት መምሪያ የተማሪ ብድር ፕሮግራሞችን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ነው።” ብለዋል።
የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስትር ሚጌል ካርዶና የባይደንን ሃሳብ ይጋራል። ካርዶና “ይህ ተጨማሪ ማራዘሚያ የኢኮኖሚው መሻሻል በሚቀጥልበት እንዲሁም ሀገሪቱ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ማገገም ስትችል ተበዳሪዎች የበለጠ የፋይናንስ ደህንነት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።” ብለዋል። ይህም “የባይደ እና ሀሪስ አስተዳደር የተማሪዎችን፣ ቤተሰቦችን እና ተበዳሪዎችን በተለይ በወረርሽኙ እጅጉን የተጎዱ ነዋሪዎችን ለመደገፍ ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ያሳየናል።” ሲል አክሏል።
የባይደን አስተዳደር እና የትምህርት መምሪያው በተበዳሪዎች ላይ ምንም አይነት ድንገተኛ የጎንዮሽ ጉዳትን ላለመፍጠር ሲባል ክፍያውን በቶሎ ለማስጀመር አልተቻኮሉም። ሆኖም የባይደን ሪፐብሊካን አቀንቃኞች ነገሩን በተመሳሳይ መንገድ አላዩትም። ምንም እንኳን ሪፐብሊካኖች መጀመርያ ትራምፕ ባጸደቀው እና ለብድር ክፍያው በተሰጠው እረፍት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከ ቀነ ገደቡ በኋላ በተደረጉ ተደጋጋሚ ማራዘምያዎች ደስተኛ አልነበሩም። አንዳንዶቹ የተማሪዎች ብድር እፎይታን “ አስደንጋጭ” ነው ሲሉ ተችተውታል።
የአርካንሳስ ሴናተር ቶም ኮተን “የፕሬዚዳንት ባይደን ተደጋጋሚ የተማሪዎች ብድር ክፍያን ማቋረጥ የትምህርት ዕዳቸውን በኃላፊነት ለሚከፍሉ አሜሪካውያን ሁሉ ስድብ ነው።” ብሏል። ኮተን የተማሪ ብድርን መክፈል የግል ሃላፊነት እንደሆነ ያምናል። ብድር የወሰዱ ተማሪዎች ግዴታቸውን መወጣት ሲያቅታቸው የዕዳው ሸክም ውሎ አድሮ በመንግስት ላይ ተመልሶ እንደሚወድቅ ያስባል።
የኮተን አስተያየት በሰሜን ካሮላይና 5ኛ ኮንግረስ አውራጃን በምትመራው የኮንግረስ አባል ቨርጂና አን ፎክስ ተስተጋብቷል። ፎክስ “ታታሪ ግብር ከፋዮች በዚህ አስተዳደር ተደጋጋሚ እርምጃዎች ተሰላችተዋል።” ብለለች። ሪፐብሊካኖች በእዳ ክፍያው መራዘም ላይ ብርቱ ተቃዋሚ ቢሆኑም እንደ ካርዶና መከራከሪያ የክፍያ ግዜው የኮቪድ -19 ተፅእኖዎች በጣም እስኪቀንሱ እንዲሁም ተበዳሪዎች ክፍያዎችን ለመክፈል አመቺ ጊዜ ላይ እስኪደርሱ ይቀጥላል።
ካርዶና “የብድር ክፍያው በቆመበት ጊዜ ለተበዳሪዎች የአዲስ ጅምር ተስፋ ለመስጠት እና ሁሉም ተበዳሪዎች የገንዘብ ሁኔታዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟሉበት የመክፈያ እቅዶችን እንዲያገኙ ለማድረግ ዝግጅታችንን እንቀጥላለን።” ብሏል። አክሎም “የትምህርት ክፍሉ ተበዳሪዎች ወደ ክፍያ ሲመለሱ ለስላሳ ሽግግር እንዲኖራቸው ለማድረግ ቁርጠኛ ነው።” ሲል ተናግሯል።