በየካቲት ወር ማገባደጃ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ መጋቢት 8 በሩሲያ ላይ ማዕቀብ አውጀዋል። ከዚያም ብዙ የአውሮፓ ሀገራት ይህንኑ ፈለግ ተከትለው ሩሲያ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል። ማዕቀቡ በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ ግዜያዊ የሆነ ትልቅ ችግር መፍጠሩ አልቀረም። ይሁን እንጂ ሊታመን በማይችል መልኩ ብዙም ሳይቆይ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በአስገራሚ ሁኔታ የሩስያ ገንዘብ ሩብል ዳግም ወደነበረበት ተመልሷል።
በሺዎች ከሚቆጠሩ በሩሲያ ላይ ከተጣሉ ማዕቀቦች ውስጥ ጆ ባይደን ዘይት፣ የፔትሮሊየም ውጤቶች፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና የድንጋይ ከሰል መግዛትን አግደዋል። ይህም የሩሲያ የመገበያያ ገንዘብ ሩብል አቅም በ 30% እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል። ገና ጦርነቱ ከተጀመረ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ መጋቢት 7 ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ150 ሩብል ይመነዘር ነበር።
የሩብል ዋጋ እያሽቆለቆለ ሲሄድ እንዲሁም ጦርነቱ ከመጋቢት ወር እስከ ሚያዝያ ድረስ እየተራዘመ ሲሄድ የፈረንሣይ የኢኮኖሚ ሚኒስትር በርኖ ለ ማይሬን ጨምሮ ሩብል በፍጥነት እንደሚያንሰራራ የገመተ አልነበረም።
በርኖ ለ ማይሬ “በሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ጦርነት ልንከፍት ነው። በሀገሪቱም የኢኮኖሚ ውድቀትን እናስከትላለን።” ሲል ተናግሯል።
ምናልባትም በሩሲያ የሚጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከረጅም ጊዜ በኋላ ምን አይነት ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል እስካሁን ያልታወቀ ቢሆንም በዚህ አጭር ጊዜ የሩስያ ሩብል ከዩክሬን ጦርነት ቀድሞ ወደነበረበት ተመልሷል።
ብዙ የአውሮፓ ሀገሮች ማዕቀብ በመጣል ከሩሲያ ጋር የሚደረገውን ትግል መቀላቀላቸውን አሳይተዋል። ይሁን እንጂ ወሳኝ የሆነውን የዘይት ምርት በማዕቀቡ ውስጥ ማካተት ቀላል ነገር አይደለም። ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን ዘይትን ማዕቀቡ ውስጥ ለማካተት ፈቃደኛ አይደሉም። በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ውስጥ ትልቁ ኢኮኖሚ የተቆጣጠረችው ጀርመን 38% የዘይት ፍጆታዋን ከሩሲያ ታስመጣለች። ስለሆነም ይሀንን ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትል ዩናይትድ ኪንግደምን እና ኤሜሪካን ለመቀላቀል ፈቃደኛ አልሆነችም።
ጦርነቱ ሀገሪቱን ለበርካታ ወጪዎች እየዳረገ ምናልባትም ፑቲን ካሰበው በላይ ቆይቷል። 4,000 የሚጠጉ ማዕቀቦችን ሩሲያ ላይ የጣለው ኔቶን ጨምሮ ሩሲያ በርካታ ማዕቀቦችን እያስተናገደች ባለችበት ወቅት በሩሲያ የኢኮኖሚ መረጋጋት መኖሩ እንዴት የሚል የግርምት ጥያቄ ያስነሳል።
ፑቲን በመጀመሪያ ዘይት በሩቤል እንዲገዛ ትዕዛዝ አቅርበዋል። ፑቲን “ክፍያን ለመቀየር የሚያስችሉ እርምጃዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመውሰድ ወስኛለሁ። የእኛ የተፈጥሮ ጋዝ ለሩሲያ ሩብል ‘ወዳጅነት ለሌላቸው አገሮች’ ይቀርባል። ” ሲል ተናግሯለ። ከዚያም የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ኢኮኖሚውን የተረጋጋ አድርጎ ለማቆየት የወለድ መጠንን ከፍ አድርጓል።
የሩብል ዋጋ በ 30% ሲቀንስ ሩሲያውያን በፍጥነት ሩብልን በዶላር ለመለዋወጥ እየሞከሩ ነበር። ነገር ግን ከ 9.5% ወደ 20% የጨመረው የወለድ መጠን በባንክ ውስጥ ለምንዛሬ መጉላላትን ለመቀነስ ረድቷል።
የሩሲያ ባንክ እንደገለጸው “የወለድ መጠን መጨመር የተቀማጭ ገንዘብን መጠን መጨመርን ያረጋግጣል። ይህም የዋጋ ቅነሳን እና የዋጋ ግሽበትን ለማመጥጠን ታስቦ ነው። እርምጃው የሚያስፈልገው የገንዘብ እና የዋጋ መረጋጋትን ለመደገፍ እና የዜጎችን ቁጠባ ከዋጋ ቅነሳ ለመታደግ ነው።” ብሏል።
600 ቢሊዮን ዶላር እና የወርቅ ክምችትን ጨምሮ ሩሲያ በአለም ትልቅ ከሚባሉት ሃብቶች አንዱ አላት። ነገር ግን በዚህ የመጠባበቂያ ሃብት ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሩሲያውያን በዓለም ዙሪያ በተለያዩ መንገዶች የያዙትን ዶላር ከንቱ ያደርገዋል። እናም ፑቲን እና ሌሎች ሀገራት ይህንን ሲገነዘቡ ከዶላር ውጪ የሆኑ ሌላ አማራጮችን ይፈልጉ ይሆናል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ሳውዲ አረቢያ ለነዳጅ ክፍያ ከቻይና በዩዋን ተቀብላለች።
ዓለም በሩብል ተመልሶ መምጣት ሊደነቅ ቢችልም የካልደርዉድ ካፒታል መስራች ዲላን ግሪስ “በገንዘብ ታሪክ ውስጥ ለውጥ የሚያመጣ እና ወደ ባይፖላር የገንዘብ ሥርዓት የሚያፋጥን” ሲሉ የማዕቀቦችን ተጽዕኖ አስቀድሞ ጠቁሟል።