የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በተጀመረ በሶስተኛው ቀን በ የካቲት 20 የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በአለም ላይ ያሉ በጎ ፍቃደኞች ዩክሬንን በማገዝ የትግል ሜዳውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበው ነበር። እንደ መደለያም በጎ ፍቃደኞቹ የተሻለ ኑሮ በዩክሬን እንደሚኖራቸው ጠቆም አድርገው አልፈዋል። ይህ ጥሪ 27 አመት በሞላው ናይጄሪያዊው ኦታህ አብርሀም በደንብ ነው የተሰማው። በትዊተር ገፁ ላይም “ልቀላቀላቸው(የዩክሬን ጦረኞችን) እፈልጋለሁ!” ሲል ፅፏል።
አብርሀም የተሻለ ኑሮ እንደሚፈልግ ከመናገሩ ባሻገር ሩሲያ በዩክሬን የምትሸነፍበት እድል አለ የሚል ሀሳብ ያለው ወይም ደግሞ በናይጄሪያ ባለው ህይወቱ ጨለምተኛ የሆነ ይመስላል። ይህም ለጦርነቱ ዝግጁ እንዲሆን ገፍቶታል።
“ጦርነት ነው። የልጆች ጨዋታ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን በዩክሬን ወታደር መሆን እዚህ ከመኖር ይሻላል። ምን አልባት ጦርነቱ ካለቀ በኋላ እዛው የምቆይበት እድል ላገኝ እችላለው። በተጨማሪም ጀግና በመሆን ከጠላት ጋር እፋለማለሁ።” ሲል ለ ቢቢሲ ተናግሯል።
የአብርሀምን ሀሳብ በ ኬኒያ ናይሮቢ ተማሪ የሆነው ኪማንዚ ካሾን አስተጋብቷል። “እዚህ ሆኜ ላገኘው የማልችለውን አሪፍ ክፍያ ዩክሬን የምትከፍለኝ ከሆነ ወደዛ ሄጄ ለመዋጋት አላቅማማም።” ብሏል።
ከ ዜሌንስኪ ጥያቄም ሆነ ከአንዳንድ በጎ ፍቃደኞች ድጋፍ ባሻገር የሌላ ሀገር ጦር ላይ መሳተፍ በብዙ ሀገሮች የሚደገፍ አይደለም። ይሁን እንጂ ዜሌንስኪ እርዳታ ከመጠየቅ አልተወገደም።
ዜሌንስኪ አለም አቀፍ የ ዩክሬን አጋዥ ቡድን ለማቋቋም ጥሪ ሲያቀርብ “የአለም ሰዎች የ ዩክሬን፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ወዳጆች በሙሉ የ ዩክሬን መከላከያን ለመቀላቀል እና ለማገዝ የምትፈልጉ የአውሮፓ እና የአለም ህዝቦች ወደዚህ መታችሁ ከ ዩክሬናውያን ጎን በመሆን ከጦር ወንጀለኛ ሩስያውያን ጋር መታገል ትችላላችሁ።” ብሏል።
በተጨማሪ የ ዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ተመሳሳይ ጥሪን አድግረዋል። “ዩክሬንንም ሆነ አለም አቀፍ ህግን ለመጠበቅ ፍቃደኛ የሆኑ የውጭ ዜጎች በ የሀገራችሁ የሚገኝ የዩክሬን የዲፕሎማሲ ተቋማትን እንድታናግሩ እጋብዛችኋለሁ። ሂትለርን በጋራ እንዳሸነፍነው ሁሉ ፑቲንንም እናሸንፈዋለን።” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አጋርተዋል።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የበጎ ፍቃደኞች የሚመዘገቡበት መካነ-ድር ቢያዘጋጅም በአለም ላይ በሚገኝ ሀገሮች ላይ በዛ ያለ ተቀባይነትን ያገኘ አይመስልም። አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም ዜጎቻቸው ሀገራቸው በቀጥታ ከተሳተፈችበት ጦርነት ውጪ በሌላ ሀገር የጦር ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፉ የሚከለክል ህግ አላቸው።
በተጨማሪም የአውሮፓ ሀገሮች ተመሳሳይ ህግ አላቸው። ጀርመን በጦርነቱ ላይ መሳተፍ የአለም አቀፍ ህግን የሚፃረር መሆኑን በመጥቀስ ዜጎችዋ በጦርነቱ እንዳይሳተፍ እና ከተሳተፉም እርምጃ እንደሚወስድባቸው አስጠንቅቃለች።
አፍሪካውያን በጦርነቱ ላይ እየተሳተፉ ቢሆንም ሀገሮቻቸው ግን ተሳትፎውን በመኮነን ላይ ይገኛሉ። የ ናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባይ ፍራንሲሳካ ናይጄሪያ ዜጎቿ በበጎ ፍቃደኝነት ተከፋይ ጦረኞች ሆነው እንዲያገለግሉ እንደማትፈቅድ ተናግረዋል። “ናይጄሪያ በየትኛውም የአለም ክፍል ተከፋይ ጦረኞች በጦርነት መሳተፋቸውን አትደግፍም። ምልመላውንም አትታገስም።” ብለዋል።
አልጄሪያም በበኩሏ የዩክሬን መንግስት ዜጎችዋን ለመመልመል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በብርቱ ተቃውማለች። በተጨማሪም የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር የሚገኘው የዩክሬን ኢምባሲ ሴኔጋላውያን ወደ ዩክሬን በማቅናት ጦርነቱን እንዲሳተፍ በመጠየቁ መገረማቸውን ገልፀዋል።
የዩክሬን ኢምባሲ የለቀቀው የፌስቡክ ፖስት ቢጠፋ ይፋዊ በሆነ መግለጫ የሴኔጋል መንግስት ድርጊቱን አውግዟል። ዜጎቹ በሴኔጋል ምድር በውጭ ሀገር ተከፋይ የሚሆኑ ጦረኞችን ከመመልመል እንዲታቀቡም አስጠንቅቋል።
ይሁን እንጂ እነዚህን ማስጠንቀቅያዎች ችላ ብለው በጎ ፍቃደኞችን ሲመዘግቡ የቆዩት የ ዩክሬን ባለስልጣናት ከ 20 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞች ከ 52 ሀገራት እንደተመዘገቡ ተናግረዋል። ይህ ቁጥር ህጋዊ የሆነውን መስመር ሳይከተሉ ዩክሬናውያኑን ለማገዝ የገቡ ሰዎችን አይጨምርም።
ዩክሬን 20 ሺህ በጎ ፈቃደኞች እንደተመዘገቡ ስትናገር ሩሲያ በበኩሏ 16 ሺህ ሰዎች እናግዛችሁ የሚል ጥሪን እንዳቀረቡ ገልፃለች በዛ ያሉት በጎ ፈቃደኞችም ከ መሀከለኛው ምስራቅ የመጡ ናቸው። በጎ ፍቃደኞቹ በጦርነቱ እንዲሳተፉም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፍቃዳቸውን ሰተዋል። ከዚህ ባሻገር ፕሬዝዳንቱ በዩክሬን በኩል በጦርነቱ ላይ ተከፋይ ተዋጊዎች መሳተፋቸው እና ምዕራባውያኑ ለ ዩክሬን እየሰጡ ያሉት ድጋፍ ከአለም አቀፍ ህግ በተቃርኖ የቆመ ነው ሲሉ ተችተዋል።