በ 2018 በኮንግረስ ታሪክ ኢልሀን ኦማር የመጀመርያዋ ሶማሌ አሜሪካዊ ሆና ስትመረጥ ሀገሪትዋ በግርምት ተንጣ ነበር። ይህን የኢልሀንን ታሪክ በሚገዳደር መልኩ በሌላኛው የፖለቲካ ፅንፍ ላይ የምትገኝ አዲስ ሱማሌ አሜሪካዊ ተቀናቃኝ ሹክሪ አብዱራህማን ብቅ ብላለች።
ኢልሀን ኦማር አሁን ላይ በሁለተኛ የስልጣን ዘመኗ ላይ ስትሆን በ 5ኛው የሚኒሶታ ቀጠና የኮንግረስ አባላት ምርጫ ላይ ለሶስተኛ ግዜ መሳተፍ እንደምትፈልግ አስታውቃለች። በ 2018 በ 78% አብላጫ የመራጮች ድምጽ መንበሯን ያጠነከረችው ኢልሀን በ2020 ደግሞ 64% የመራጮችን ድምጽ አሸንፋለች። ይሁን እንጂ በዚህ የሶስተኛ ዙር ምርጫ ለመሳተፍ ባቀደችበት ወቅት ከተቀናቃኟ ሹክሪ አብዲራህማን የገጠማት ተቃውሞ በአጋማሽ ዘመን ምርጫዎች ላይ እንኳን የኢልሃንን ድምጽ እጅግ ዝቅ ያደረገ ነው።
ልክ እንደ ኢልሃን ኦማር ሁሉ ሹክሪ የተወለደችው በሶማሊያ ሲሆን ሀገርዋ በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመስበት ወቅት በኬንያ ስደተኛ ነበረች። ከኢልሀን በተቃራኒ የሪፐብሊካን ተወካይ የሆነችው ሹክሪ ወደ አሜሪካ የሄደችው በአስራዎቹ የአድሜ ዘመንዋ ሲሆን በ አሜሪካ መከላከያ ውስጥም አስር አመት አገልግላለች።
ሹክሪ ወደ ፖለቲካው መድረክ እንድትገባ የተነሳሳችው ለ 10 አመታት ሰራዊቱን ባገለገለችበት ወቅት ነው። “ሠራዊቱን ከለቀቅኩ በኋላ ሁል ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ሆኜ አገሬን በተለያየ ኃላፊነት ማገልገል እፈልግ ነበር።” ስትል ተናግራለች። አስከትላም “አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገሬን ለማገልገል የምጠብቀው ምንም ተጨማሪ ጊዜ እንደሌለ ተረድቻለሁ።” ብላለች።
ሹክሪ በኢልሃን ላይ የሚነሱ አከራካሪ ጉዳዮችን አንስታ ሞግታለች። መቆም ያልቻለው ብጥብጥ፣ የፖሊስ የገንዘብ ድጋፍ እገዳ እና የ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ እንቅስቃሴ በምሳሌነት አንስታለች። “የብላክ ላይቭስ ማተር ተሟጋቾች የሆኑ በርካታ መልካም ሰዎች ቢኖሩም ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ አካላት ግን ብዙም ግድ ሊሰጣቸው አልቻለም።” ብላለች። የፖሊስ የገንዘብ ድጋፍን መከልከል የሚለውን የኢልሃንን አቋም እንደማትጋራም ገልጻለች።
ሹክሪ “ኢልሃን የፖሊሶች የገንዘብ ድጋፍ መቋራጥ ላይ አፅንኦት ሰታ እንደምትሰራ እና ይህም የህይወት ተልዕኮዋ መሆኑን በመሀላ አፅንታዋለች” ትላለች። አስከትላም “በዚህ አመት በሚኒኣፖሊስ የተመዘገበው ሁከት እና ብጥብጥ ከአለፉት ግዜያት ሁሉ ከፍ ያለ ነው። በዚህ ከተማ የሚመዘገበው የወንጀል ሪፖርት መጠን ከ 2021 ጀምሮ 17 በመቶ ጨምሯል በተጨማሪም በከተማው ውስጥ በሚፈፀሙ ግድያዎች ሳያባሩ እንደቀጠሉ ናቸው።” ስትል ለፎክስ ኒውስ ገልፃለች።
ነገር ግን ኢልሀን ለወንጀል መስፋፋቱ የፖሊስ ባልደረቦችን ተጠያቂ ናቸው ስትል የያዘችው ፅኑ አቋም የማናወጥ ሆኖ ቆይቷል። በፖሊሶች አሰራር የተሰላቸችው ኢልሀን መሰርታዊ ለውጥ እንዲመጣ መወትወቷን ቀጥላለች። “ፖሊስ ለቢሮው የገባውን ቃለ መሀላ አለመፈጸም መርጧል።” ስትል ትተቻለች።
ኢልሀን የሚተቿት አካላት የፖሊስ ሀይሉ አሁን ባለው ሁኔታ ቢቀጥል የህብረተሰቡን ሰላም ማስጠበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ ባሻገር በፖሊስ እጅ የሚሞቱ ንፁህ ዜጎችን ማስቆም የማይችልበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ማየት እንደተሳናቸው ታምናለች። ለዚህም ነው “መሰረቱ የበሰበሰ አመራርን እንደ አዲስ መገንባት እንጂ ማደስ አይቻልም!” የምትለው።
ኢልሃን ከ100 በላይ ህጎች በማስተዋወቅ፤ ስምንት ረቂቆች በህግ ማዕቀፍ እንዲገቡ በማድረግ እና 48 ረቂቅ ህጎችን በምክር ቤቱ በኩል በማፅደቅ የስልጣን ዘመኗ ስኬታማ ቢሆንም የሪፐብሊካን ፓርቲዎች በበኩላቸው በሰፊ ሁኔታ በከተማዊ የሚገኘውን የሶማሊ ህዝብ የሚመለከቱ ቁልፍ ጉዳዮችን ለመፍታት ከመሞከር አልተቆጠቡም።
አብዛኞቹ ወግ አጥባቂ አመለካከት ያላቸው የሶማሊያ ማህበረሰቦች ምንም እንኳን ኢልሀን የያዘቻቸውን አንዳንድ አቋሞች የማይደግፉ ቢሆንም ብቸኛዋ ሶማሌ-አሜሪካዊ በነበረችበት ግዜ ድምፃቸውን ለ እርስዋ ከመስጠት አልተቆጠቡም። ለግብረሰዶማዊን የማህበረሰቡ ክፍሎች የሰጠችው ድጋፍ እና ከስኳድ ቡድን ጋር ያላት ግንኙነት (በዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ ያለ ተራማጅ ቡድን) አባል መሆኗ በእነዚህ ወግ አጥባቂ ሱማሌያውያን የሚደገፍ አልነበረም። አሁን ላይ ግን የሱማሌያውያኑን እሴት እና እምነት እንደምታከብር ማሳየት የቻለችው አዲስዋ የኢልሀን ተቀናቃኝ መምጣት ሁኔታዎቹን ከመቀየራቸው ባሻገር ለኢልሀንም ከበድ ተቃውሞ እንደሚገጥማት ይጠበቃል።
የቀኝ ክንፍ አባላት እና ፎክስ ኒውስ ሹክሪ በኦማር ላይ ለምታቀርበው የሰላ ትችት መድረኩን ከማመቻቸት ወደ ኋላ አላሉም። ሹክሪ ለፎክስ “እኔ ማህበረሰቤን እና ቀጠናዬን ሙሉ በሙሉ ችላ ካለችው ከኢልሃን ኦማር ጋር እወዳደራለሁ። ይህ ቸልተኝነት ያስፈራኛል! አስተማማኝ መሸሸግያ በሆነኝ ሀገሬ ላይ ያሉኝን ሶስት ልጆች ማሳደግ እፍለጋለሁ። ሀገሬ በልጅነቴ ደህንነት እንዲሰማኝ አድርጋኛለች ይህንንም ለልጆቼ ማቆየት እፈልጋለሁ።” ስትል ለፎክስ ኒውስ ገልጻለች።