እጅግ ፈጣን በሆነ መንገድ የሚተላለፈው አዲሱ የ ኮቪድ 19 ዝርያ አሚክሮን በ ጥቂት ወራት በ አሜሪካ 132,646 በቫይረሱ የተጠቁ ህመምተኞች በሆስፒታል እንዲታከሙ በማድረግ በ ፈረንጆቹ ጃንዋሪ ወር ላይ ተይዞ የነበረውን የ 132,051 ከፍተኛ የሆስፒታል ታካሚዎች ቁጥር እንዲያልፍ አድርጎታል።
ይህ የ ኮቪድ 19 ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር መበራከት የተለያዩ የስፖርት ፕሮግራሞች፣ የጉዞ እቅዶች እንዲሁም የ ስራ ዝግጅቶችን ከማቋረጥ እስከ ማስተጓጎል አድርሷል።
በተለይም ከረጅም ግዜ የመደበኛ የትምህርት ስርአት ርቀው የቆዩ ተማሪዎች እና መምህራን ወደ ትምህርት ለመግባት በጓጉበት በዚህ ወቅት ኦሚክሮን ተስፋቸውን አጨልሞታል። በሺህ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ላይ የትምህርት መጀመርያ ግዜውን ያስተጓጎለ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ከመደበኛው የትምህርት አሰጣጥ ይልቅ በቴክኖሎጂ የተደገፉ መንገዶችን እንዲከተሉ አስገድዷል።
የነጩ ቤተመንግስት ባለስልጣናት እና የከተማ ከንቲባዎች አስፈላጊው የጥንቃቄ መንገድ እየተከተልን ትምህርት ቤቶች መከፈት አለባቸው የሚል አቋም ቢይዙም በአዲሱ አመት መግቢያ የመጀመርያዎቹ ወራት በመላ ሀገሪቱ ከ 2750 በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቆይተዋል።
ፕሬዝዳን ጆ ባይደን ለሚዲያ ሰዎች ገለፃ ባደረጉበት ወቅት “ኮቪድ 19 አስፈሪ ነው ነገር ግን ሳይንስ ከዚህ በላይ ግልፅ ነው። ከሌሎች ቦታዎች በተሻለ አስፈላጊውን የጥንቃቄ መንገድ ከተከተልን ህፃናት በትምህርት ቦታቸው ላይ ሰላም ናቸው።” ሲሉ ተደምጠዋል።
ትምህርት ቤቶች ሳይዘጉ ነባር የመማር እና የማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ወላጆች እና አስተማሪዎችም ቢሆኑ አሁን ላይ ያለው የጤና አጠባበቅ ተማሪዎችንም ሆነ ሰራተኞችን ከ አሚክሮን ዝርያ ለመጠበቅ በቂ ነው ወይ? የሚለው ጭንቅ ሆኖባቸዋል። የ ኒው ዮርክ ከንቲባ የሆኑት ኢሪክ አዳምስ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን ለ አንድ ሚሊየን ተማሪዎች የ ኮቪድ 19 መመርመርያ ኪቶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ይህን ቁጥር በእጥፍ በመጨመር በየትምህርት ቤቱ ምርምመራዎችን ለማድረግ ወስነዋል። እኒሁ ከንቲባ አንድ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት በጎኙበት ወቅት “ለልጆቻችን ሰላማዊ ስፍራ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን አፅንኦት መስጠት ያስፈልጋል።” ብለዋል። ይሁን እንጂ ወላጆች አሁን ድረስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ገብቷቸዋል።
በ ኒውዮርክ የ 9 አመት ልጅ እናት የሆነችው ትሪሻ ልጅዋ ትምህርት ቤት ሆነም አልሆነም ጭንቀት እንደማይለቃት ትናገራለች ሆኖም በትምህርት ቤት ከእኩዮቹ ጋር ቢሆን እንደሚሻለውም ታምናለች።
“ከትምህርት ቤት ውጪ ቫይረሱ ሊዘው ይችላል። ስለዚህ ምን ማድረግ እንችላለን? የትምህርት ተቋማቱን መተቸትም አልችልም። ያቅማቸውን የተሻለ ነገር ለማድረግ እየጣሩ ነው።” ብላለች!
የመምህራን ህብረት በበኩሉ ከንቲባው ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትን ግዜ በአንድ ሳምንት እንዲያራዝሙት ጠይቋል። በዛ ያሉ ወላጆችም ቢሆኑ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ከማቅማማት አልፎ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ አድርገዋል። በኒው ዮርክ ሮችስተር 40% የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ቦታቸው ላይ አልተገኙም።
በ ኒው ሀምፕ ሻየር ልጅዋን በ ጃንዋሪ መጀመርያ ወደ ትምህርት ለመላክ ወስና የነበረችው ሜጋን የቫይረሱ አስደንጋጭ የሆነ መዛመት ሀሳብዋን እንድትቀይረው አስገድዷታል። “ቫያረሱ በዚህ መልኩ እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ተረጋግተን ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አንችልም።”ብላለች።
የሀገሪትዋ ሶስተኛው ትልቁ የትምህርት ቀጠና የሆነው ቺካጎ በአስተማሪዎች ጠበቅ ያለ የኮቪድ 19 መከላከያ ጥያቄ መሰረት የህዝብ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ከመምህራን ህብረት አባላት መሀከል 73% የሚሆኑት መደበኛው ትምህርት ተዘግቶ ወደ ርቀት ትምህርት እንቀይር የሚለው ላይ ቢስማሙም የመንግስት ባለስልጣናት ግን ትምህርት ቤቶች ይዘጉ በሚለው ላይ እንደማይስማሙ በመግለፅ ለማስተማር ፍቃደኛ የሆኑ አስተማሪዎችን በመያዝ መደበኛ የትምህርት ፕሮግራሞቹን እንደሚቀጥል ተናግሯል። ቀስ በቀስ ባለው የሰው ሀይል መጠን ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱም ገልፅዋል።
በሚኒሶታ በዛ ያሉ ትምህርት ቤቶች መደበኛ ትምህርት እየሰጡ ቢሆንም የትምህርት ተቋማቱ መሪዎች እንደገለፁት ከሆነ በቫይረሱ እየተያዙ ያሉ መምህራን እና ተማሪዎች ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እየጨመረ ነው። በቫይረሱ የተጠቁ መምህራን ቁጥር በመብዛቱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለሶስት ሳምንት መደበኛ ትምህርታቸውን በመተው ወደ ርቀት ትምህርት ሲሸጋገሩ መደበኛ ትምህር እየሰጡ ያሉ ትምህርት ቤቶች ቢሆኑም ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ግዜ በኋላ ያለውን ፕሮግራም ተማሪዎችን የሚያመላልሱ ሹፌሮች በቫይረሱ በመያዛቸው ባጋጠማው የባስ አሽከርካሪ እጥረት ለማቋረጥ ተገደዋል።
በዚህ አስደንጋጭ የኦሚክሮን መዛመት እና በትምህርት ቤቶች መከፈት አለመከፈት ላይ ጥያቄ ውስጥ ቢሆኑም ወላጆች እና የትምህርት ቤቶች አስተዳደሮች ትምህርት ቤቶችን ለትንሽ ግዜ መዝጋት መፍትሄ ነው አይደለም የሚለውን ከመጠየቅ አልፎ መቋጫ ላልተገኘለት የኮሮና ምስቅልቅል ቋሚ መፍትሄ ፍለጋ ላይ ናቸው።
የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆነው ዳንኤል ዶሚኒክ እንደሚናገረው ከሆነ “አሁን የሚያሳስበን ይህን ቫይረስ ዝርያ ብናልፈው እንኳ ቀጣይ አዲስ ዝርይያ ቢመጣ ምን ልንሆን ነው? አዲስ ዝርያ ዳግም ተከስቶ ድጋሚ በዚህ መልኩ ትምህርት ቤቶች እስኪዘጉ ለትንሽ ግዜ ልናስተምር ነው?” ይላል።
የ ዶሚኒክ ፍራቻ በሀገሪቱ ሁሉ ሲስተጋባ ተስተውሏል። በ ቫይረሱ መከሰት የተስተጓጎለው የተለመደው የአኗኗር ዘይቤ ወደነበረበት ሳይመለስ አዳዲስ ዝርያ እየመጣ መነቃቃት የጀመረውን አኗኗር ድጋሚ ሲያቀዘቅዘው ተስተውሏል። አሁንም ቢሆን የተጠና እቅድ ተነድፎ መንቀሳቀስ የማይቻል ከሆነ አዲስ ዝርያ በመጣ ቁጥር ምስቅልቅሉ ይቀጥላል።