ከ 2020 ጀምሮ ከቀናት በፊት ያገባደድነውን የ 2021 ጨምሮ መቋጫ ባላገኘንለት ወረርሽኝ እየተሰቃየን ቆይተናል። በወረርሽኙ የሚያዙ የሰዎች ቁጥር መቀነስ እና ሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ ህመምተኞች ቁጥር የተወሰነ መሻሻል እያሳየ ባለበት ጊዜ አዲስ የወረርሽኙ ዝርያ ተፈጥሯል። ኦሚክሮን በ2021 መገባደጃ ላይ የተከሰተ ሲሆን በ 2022 መጀመሪያ ደግሞ ኦሚክሮን BA.2 “ስውር ኦሚክሮን” በመባል የሚታወቀው አዲስ ዝርያ እየተንሰራፋ ይገኛል።
የተላላፊ በሽታ ሊቅ የሆነው ካሜሮን ዎልፌ ኦሚክሮን BA.2ን ከኦሚክሮን BA.1 ጋር በማነጻጸር “አንድ ቤተሰብ ውስጥ እንዳሉ ወንድማማቾች ናቸው ማለት ይቻላል። አንዳንድ ጥቃቅን ልዩነቶች አሉ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ዘረመል በሁለቱም ውስጥ ይገኛሉ።” ብሏል።
ኦሚክሮን BA.2 ለመጀመሪያ ግዜ ኦሚክሮን BA.1 በተገኘበት ተመሳሳይ ቦታ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተገኘ ሲሆን በፍጥነት ወደ እስያ እና አውሮፓ ሀገራት ሊስፋፋ ችሏል። ለምሳሌ ዴንማርክ በቀን ከ 40,000 በላይ የሆኑ የቫይረሱ ተጠቂዎችን እያስተናገደች ሲሆን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየታገለች ነው። ከጥር ወር ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ከወረርሽኙ ተጠቂዎች ውስጥ 50% የሚሆኑት በBA.2 ምክንያት ነው ሲል ስታቴንስ ሴረም ኢኒስቲትዩት ተናግሯል። በእንግሊዝ እና በጀርመን 5% የሚሆኑ የBA.2 ተጠቂዎች ተገኝተዋል።
አሜሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀላቀል የመጨረሻዋ ሀገር ብትሆንም በአለም ዙሪያ ካሉ ሀገራት በበለጠ ፍጥነት ሊሰራጭ እንደሚችል ተገምቷል። አዲሱ ተለዋጭ ቫይረስ በካሊፎርኒያ፣ ቴክሳስ እና ዋሽንግተን ውስጥ ተገኝቷል። ምንም እንኳን ወረርሽኙ አሁን ላይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም በሚቀጥለው ወር ስርጭቱ ይጨምራል የሚሉ ስጋቶች እየተሰነዘሩ ናቸው።
በካሜሮን ዎልፌ እንደተጠቀሰው ሁለቱ የኦሚክሮን ዝርያዎች በጣም ተመሳሳይ ናቸው። የሱን ሀሳብ በመጋራት በበርን ዩኒቨርሲቲ ኤፒዲሚዮሎጂስት የሆነችው ኤማ ሆድክሮፍት ሁለቱ ተለዋጮች “በእኔ እምነት እንደ ወንድማማች እና እህታማቾች ናቸው። የተለያየ ነገር አላቸው ግን ግልጽ የሆነ ተዛማጅነትም አንደዛው።” ስትል ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥታለች።
ካላቸው ልዩነቶች ውስጥ አንዱ የአዲሱ ተለዋጭ በፍጥነት የመተላለፍ አቅም ነው። ምንም እንኳን አዲሱ ተለዋጭ የበለጠ ተላላፊ ሊሆን ቢችልም የሳን ፍራንሲስኮ ዩኒቨርሲቲ መምህር ቺን-ሆንግ እንደተናገረው “ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ከBA.1 ጋር ሲነጻጸር በBA.2 የተያያዙ ህመምተኞች ሆስፒታል የሚያስኬድ ጠንከር ያለ ጉዳት አይደርስባቸውም። ይህ ሊለወጥ ይችላል ነገር ግን እስካሁን የምናውቀው ነገር ነው” ሲል ገልጿል።
እስካሁን በቫይረሱ ምከንያት የተጀመረ የርቀት ትምህርት ወይም ተጨማሪ የስራ ቦታዎችን መዝጋት ባይኖርም ሶስተኛውን የኮቪድ19 ክትባት እንዲወስዱ ጫና እየተደረገ ይገኛል። ከዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሶስተኛውን ክትባት መውሰድ በአዲሱ ወረርሽኝ የመያዝ እድልን ከ60-70 በመቶ ይቀንሳል። ብሏል።