በታህሳስ 2 ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገፃቸው ላይ በአለም ዙርያ ለሚገኙ አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን በጥር 7 ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ግብዣቸውን አስተላልፈዋል። ይህ ግብዣ የሰላም ተስፋን ያነገበ እና የዲያስፖራው ማህበረሰብም ለእናት ሀገሩ አለኝታነቱን እንዲያሳይ ያለመ ቢሆንም ወደ ሀገር ከገቡ በኋላ የተከሰቱ አንዳንድ ጉዳዮች መለምለም ጀምሮ የነበረውን ተስፋ ማጨለማቸው አልቀረም።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በፌደራል መንግስት እና በህውሓት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ድርድር እንደሚደረግ እንደተናገሩ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መስፍን ተገኑ ተናግረዋል። አቶ መስፍን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ሲጠቅሱ “ ምክንያትያዊ የሆነ የሀገሪቱን አንድነት ጥቅም የሚያስቀድም ድርድር ይኖራል።” ብለዋል። በሌላ በኩል የህውሓት መሪ የሆኑት ዶ/ር ደብረጺዮን ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ጀምረናል ብለዋል።
የቢቢሲ አፍሪካ ባልደረባ የሆነው ዊል ሮዝ በትዊተር ገፁ ላይ እንዳሰፈረው “የህውሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ለቢቢሲ ከአዲስ አበባ መንግስት ጋር መነጋገር መጀመራቸውን ገልፀዋል። በሶስተኛ አካል እየተደረገ ያለው ይህ ድርድር ተስፋ ሰጪ ቢሆንም የተሻለ ፍሬ እስኪያፈራ በመጠባበቅ ላይ ነን።” ብለዋል።
ከዚህ ድርድር ጀርባ ማን እንዳለ እና በማን እየተመራ እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ሆኖም አንዳንድ እየተናፈሱ እንዳሉ መረጃዎች ከሆነ አሜሪካ ወይም ኬንያ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ የድርድር ወሬ እየተናፈሰ ባለበት በዚህ ወቅት በአማራ እና አፋር ክልሎች የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ይሁን እንጂ በ ትግራይ የሚኖሩ 6 ሚሊየን ነዋሪዎች ዛሬ ድረስ ከሁለንተናዊ እንቅስቃስያቸው ታግደዋል። ይህንን ሁኔታም ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረ እየሱስ “ገሃነም” ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፌደራል መንግስት በሰላማዊ ድርድሩ ላይ ፅኑ መሆኑን ለማሳየት በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ “የህዝቡ ስቃይ እንዲያበቃ ለማድረግ የሚያስችለውን የትኛውንም እንቅስቃሴ እናደርጋለን!” ብለዋል ሲሉ አቶ መስፍን ተገኑ ተናግረዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ በትግራይ ክልል የነበረውን የኔትዎርክ አውታር ወደነበረበት ለመመለስ እየሰሩ መሆናቸውን እና ይህን ለማሳካትም 7 ቢሊዮን ብር በጀት መድበው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የህወሓት መሪዎችን ጨምሮ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከእስር ተፈትተዋል ይህ በህዝቡ ዘንድ የተለያየ ስሜትን ፈጥሯል።
የድርድር ወሬ እየተነሳ ባለበት እና በመንግስት በኩልም ለድርድሩ መሳካት የተደረጉ የሚመስሉ እርምጃዎች ባሉበት በዚህ ወቅት ህውሓት የድርድሩን ተፈፃሚነት ጥያቄ ውስጥ እንዲከት በሚያስገድድ መልኩ በአፋር ክልል ወታደራዊ ጥቃት ፈጽሟል። ለትግራይ አዋሳኝ በሆነችው የአባላ ከተማ ነዋሪዎች ከጥር 14 ጀምሮ በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የተኩስ እሩምታ እንደነበር መስክረዋል። ተኩሱ ትምህርት ቤቶች፣ መስጂዶች እና መኖሪያ ቤቶችን አውድሟል። ከዚህም አልፎ ወደ ትግራይ የሚገቡ የእርዳታ መንገዶች እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል።
በጥቃቱ ወቅት በቦታው እንደነበሩ የሚናገሩት የአባላ ከተማ ነዋሪ ኡመር አሊ “የህውሃት ወታደሮች ከተራራ ላይ ሆነው ሲተኩሱብን ነበር። ይህ ጥቃት የአፋር ክልል ልዩ ሀይሎችን አዳክሟል። ይህን መዳከም ተከትሎ የህውሀት ሀይል ወደ ከተማዋ እየተቃረበ በመምጣቱ የአፋር መንግስት የከተማው ነዋሪዎች ጦርነቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል። የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ጦርነቱን ሲቀላቀሉ የህውሀት ወታደሮቹ ወደ ኋላ አፈግፍገዋል።” ሲል ገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኢትዮጲያ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር የህወሓትን ትንኮሳ አስመልክቶ ተወያይቷል። የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተመስገን ጥሩነህ የመከላከያ ሰራዊት እርምጃ እንዲወስድ አቅጣጫ መቀመጡን ቢናገሩም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በ ድርድሩ ጉዳይ ተስፋ ሰጪ ጭላንጭል የታየ ቢመስልም በአፋር የተደረገው ጥቃት ግን ለስኬቱ እንቅፋት ሳይሆን አይቀርም። ለጥቃቱ መከላከያ ምንም አይነት አፀፋዊ እርምጃን አልወሰደም የፌደራል መንግስቱም ቢሆን ድርድሩን በማስመልከት የትኛውንም ይፋዊ መግለጫ አልሰጠም።