እ.ኤ.አ. በ1934 በጀመረው የቤልጂየም የጌንት-ቬልጌም ውድድር ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ ሽልማቱን መውሰድ ችላለች። በመጋቢት ማገባደጃ በተደረገው ውድድር የ 21 አመቱ ኤርትራዊ ቢኒያም ግርማይ የሻምፒዮንነት ዘውድን ተቀዳጅቷል።
የ 21 አመቱ ቢኒያም ውድድሩን ያደረገው ከእርሱ እጅግ የላቀ ልምድ ካላቸው ከፍተኛ ተፎካካሪዎች ጋር ነበር። በውድድሩ ከተሳተፉት ሌሎች ብስክሌተኞች መካከል ፈረንሳዊው ክሪስቶፍ ላፖርቴ እንዲሁም ቫን ጌስቴል ድሪስ እና ጃስፐር ስቱይቨን ከቤልጂየም ይገኙበታል።
ቢኒያም ውድድሩ በድል ካጠናቀቀ በኋላ “(ድሉ) በአለም ላይ ያለንን አቅም ለማሳየት ለእኔ፣ ለአህጉሬ፣ ለኤርትራ እና በተለይም ለጥቁር ብስክሌት አትሌቶች ትልቅ ተምሳሌት ነው።” ብሏል። አስከትሎም “የማይታመን እና አስገራሚ ነው። ይህን አልጠበቅኩም።” ሲል ደስታውን ገልጿል።
ምንም እንኳን እሱ ይህን ድል ባይጠብቅም አስደናቂ ብቃቱን ግምት ውስጥ ያስገቡ ደጋፊዎቹ ግን ድሉን ተስፋ አድርገው ሊሆን ይችላል። ቢኒያም እ.ኤ.አ. በ 2018 የ UCI የዓለም ብስክሌት ማእከል ልማት ፕሮግራምን ከተቀላቀለ ግዜ ጀምሮ አድናቆት አየተቸረው ይገኛል።
በሁለት አመታት ውስጥ ብቻ በአፍሪካ በሁለት ታላላቅ ውድድሮች አራት ደረጃዎች አሸንፏል። በአፍሪካ መካከለኛው ምዕራብ የባህር ጠረፍ ላይ በምትገኘው ጋቦን ውስጥ በሚደረገው የላ ትሮፒካል አሚሳ ቦንጎ አመታዊ ውድድር ሶስት ጊዜ አሸንፏል። በተጨማሪም በቱር ሩዋንዳ አንድ ጊዜ ድል ተጎናጽፏል።
ከዚህ በተጨማሪ ቢኒያም በአሁኑ ጊዜ በ UCI የክዊክ ስቴፕ አልፋ ቪናይል ቡድን ተወዳዳሪ የሆነውን ቤልጂየማዊውን ብስክሌተኛ ሬምኮ ኤቬኖፔል መርታት ከቻሉ ጥቅት ብስክሌተኞች አንዱ ሆኗል። ቢኒያም ሬምኮን ያሸነፈው በ ኦውቤል ቲምስተር ስታቬሎት ውድድር ላይ ነበር።
ቢኒያም ብዙ ውድድሮችን በማሸነፍ በአውሮፓ እና አፍሪካ ከበሬታን በማግኘት ብቻ አልተገታም ይልቅስ በ 2021 UCI ባዘጋጀው ከ 23 አመት በታች የሆኑ ብስክሌተኞች ውድድር ላይ የ ብር ሜዳልያ ተሸላሚ በመሆን በድጋሚ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ አትኩሮትን መሳብ ችሏል።
ሁለተኛው የውድድር ግዜ ቱር ኦፍ ፍላንደርስ በሚያዝያ 3 በቤልጂየም ቢደረግም ቢኒያም ግን አልተሳተፈም። “ለሦስት ወራት ያህል ሀገሬ አልሄድኩም” ብሏል።
ነገር ግን በሀገር ውስጥ ሆኖ ለቀጣዩ ትልቅ ውድድር እንደሚዘጋጅ አሳውቆ ነበር። “አሁን ወደ ሀገሬ እየሄድኩ ነው። እንዲሁም ለ’ጊሮ ዲ ኢታሊያ’ እየተዘጋጀሁ ነው”። ብሏል። ጊሮ ዲ ኢታሊያ በጣሊያን ውስጥ በዋነኛነት የሚካሄድ ዓመታዊ በርካታ መድረክን የያዘ ውድድር ነው። በዚህ አመት ከግንቦት 6 እስከ ግንቦት 29 ተካሂዷል።
ይሁን እንጂ ቢንያም በውድድሩ ላይ ወደ ድል እየተጠጋ በነበረበት ወቅት በአስረኛው ዙር ላይ ያገኘውን ድል በማክበር ላይ እያለ አደጋ አጋጥሞታል። ድሉን ለማክበር ይከፍተው የነበረው ሻምፓኝ ክዳን በአጋጣሚ ወደ አይኑ በመወርወሩ እና በግራ አይኑ በውስጥ በኩል በፈሰሰው ደም በ ውድድሩ አስራ አንደኛ ዙር ላይ መሳተፍ አልቻለም።
ቢኒያም በቀጣይ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 17 በ ኮፐን ሀገን ተጀምሮ በ ፓሪስ በሚያልቀው የ ቱር ዲ ፍራንስ ውድድር ላይ ይሳተፍ ይሆናል።