ባለፉት ስድስት ወራት በምዕራብ ዋሽንግተን ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ በኢስላማዊ ተቋማት ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ የህብረተሱ አባላት አንድነትን፣ ጥንካሬን፣ እንዲሁም አልበገር ባይነትን ለማሳየት የአንድነት ቀንን በአሜሪካ ወጣት ሙስሊሞች ማእከል ውስጥ አካሄደዋል።
ጥቃቱ ከደረሰባቸው አራቱም ኢስላማዊ ተቋማት የተውጣጡ የህብረተሰብ አባላት በመአከሉ በመሰብሰብ አንድ ላይ ጠንካራ እንደሆኑ አሳይተዋል። ከሙስሊሙ አባላት በተጨማሪ ተመሳሳይ የጥላቻ ጥቃት የደረሰባቸው የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ተቋማት ጨምሮ በርካታ ተሟጋች የመንግስት አካላት ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። የቡሪን ፖሊስ አዛዥ፣ የከተማው ምክር ቤት አባላት እና የዋሽንግተን ገዢ ጄይ ኢንስሊ በስብሰባው ታድመዋል።
የዋሽንግተን አመራር “እዚህ የተገኘነው በዋሽንግተን ውስጥ በአሜሪካ ሙስሊም ላይም ይሁን በማነኛውም ግለሰብ ላይ የሚደርስ ጥቃት በከተማዋ ውስጥ ያለውን ሁሉንም ሰው እንደማጥቃት ነው።አንዳንድ ግለሰቦች በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ፍርሃትን ለመጫር ሞክረዋል” ብሏል። አመራሩ ህብረተሰቡ ጥላቻን አጥብቆ እንዲከላከል ጥሪ አስተላልፏል። በርካታ ታዳጊ ታዳሚያን በነበሩበት በዚህ ዝግጅት አመራሩ “እነዚህ ህጻናት የወደፊት የዋሽንግተን ተስፋ ናቸው።” ብሏል።
በዋሽንግተን ውስጥ በተለያዩ የእምነት ተቋማት ላይ አያሌ የጥላቻ ወንጀሎች ተከስተዋል። ባለፈው አመት ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት፣ ምኩራቦች፣ የሲክ ማእከላት እና የእስልምና ማዕከላት የነዚህ ወንጀሎች ሰለባ ሆነዋል። ከተለያዩ ድርጅቶች የተውጣጡ ተናጋሪዎች በየድርጅታቸው ስለተከሰቱት ክስተቶች ተናግረዋል።
የሲክ ማህበረሰብ አባል አንድ ግለሰብ እንዴት ወደ ሲክ ማዕከል ሰብሮ እንደገባና ቦታውን እንዳወደመው ተናግሯል። ከኦሎምፒያ ኢስላማዊ ማዕከል የሆነ ከሪም በማዕከሉ ላይ አንድ ግለሰብ ፈንጂ እንደጣለ ተናግሯል። ከታኮማ ኢስላማዊ ማዕከል የሆነው ናስር ምዕመናን በመስጂዱ ውስጥ ሆነው የሌሊት ሰላት ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት አንድ ሰው መስጂዱን ለማቃጠል እንደሞከረ ተናግሯል። ወንጀለኛው የመስጂዱን የተወሰነ ክፍል ማቃጠል ቢችልም መንገደኞች እሳቱ ከመስፋፋቱ በፊት ስግደት ሊፈጽሙ የተሰበሰቡ ሰዎች እንዲያስቆሙት መናገር ችለዋል
በተከታታይ በመአከላቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች የተቋማቱን አባላት ይህ የጥላቻ ወንጀል በቀጣይ የት ሊፈጠር ይሆን በሚል ማስጨነቁ አልቀረም። የአሜሪካ ወጣት ሙስሊሞች ማእከል ኢማም የሆኑት ዶክተር ያህያ ሱፊ በማእከሉ ላይ ከተፈጠረው ጥቃት በኋላ በነበሩት ቀናት ከዛ ቀደም ይፈጽሙ የነበሩትን በጠዋት ላይ መስጂድ ውስጥ እንደመገኘት ያሉ ልማዶችን ለማቆም ተገደዋል። አንድ ቀን አንድ ግለሰብ ወደ መኪና ማቆሚያው መኪናውን በሃይል ነድቶ ከህንጻው ዳር ጋር አጋጭቶት የሄደ ጊዜ ኢማሙ መስጅድ ውስጥ ብቻቸውን ነበሩ።
ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በፍርሃት ከመቀመጥ ይልቅ አንድ ላይ በመሆን ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሯል።ዶ/ር ያህያ “ልባችን ውስጥ ፍርሃት እንደሚጭሩ ቢያስቡም ይልቁንም አጋሮችና ወዳጆችን አምጥተውልናል። ክፉ ነገር መልካም ነገርን ሊበግር እንደማይችል እንዲሰማን አድርገውናል።” ሲሉ ከተለያየ እምነት፣ ጎሳና አስተዳደግ የመጡ ማህበረሰቦች በነበሩበት በዝግጅቱ ላይ ተናግረዋል።
በአንድነት ስብሰባው ላይ ተናጋሪዎቹ በሃገሪቷ እንዲሁም በአለም ላይ የደረሱ በርካታ የጥላቻ ወንጀሎችን አስታውሰዋል። የአንድነት ቀኑ የተካሄደው በአትላንታ ስፓ ውስጥ በስድስት እስያውያን ላይ አሰቃቂ ግድያ በተፈፀመበት የአንድ አመት በዓል ላይ ነው። ተናጋሪዎቹ የአንድነት ቀን በኒውዚላንድ በርካታ ሙስሊሞች ላይ አሰቃቂ ግድያ የተፈፀመበት የሶስት አመት የምስረታ በዓል ማግስት መሆኑን ተናግረዋል።
በዋሽንግተን ውስጥ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ያሉት እነዚህ የጥላቻ ወንጀሎች በጣም ከተጠላና የተንኮል ቦታ እንደመጡ ከማየት በስተቀር የማህበረሰቡ አባላትማድረግ የሚችሉት ነገር የለም። ነገር ግን በተባበረ ክንድ ለመታገልም ተዘጋጅተዋል። አኒላህ አፍዛሊ “ፍቅራችን፣ አንድነታችን፣ አንድነታችን፣ ሁሌም ከዚያ ጥላቻ ይበልጣል።” ብላለች።
ነገር ግን ጥላቻን በጥላቻ ከመዋጋት ይልቅ እነዚህ ተቋማት ህብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ላይ፣ ጥላቻን ማውገዝ፣ ባለሥልጣናት ዜጎችን እንዲጠብቁ በተለይም ሰላምን የሚሰብኩ የሆኑትን የማህበረሰብ ማዕከላት መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርገዋል። ይህንን ሃሳብ የሲያትል ፍርድ ቤት ኮሚሽነር እና የኢሚግሬሽን እና የስደተኞች ጉዳይ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ሃምዲ መሀመድ ተጋርተውታል።
ከታላቅ ተናጋሪዎች መካከል አንዷ የሆነችዋ ሃምዲ የተመረጡ ባለስልጣናት እነዚህን የማህበረሰቡን ማዕከላት ለመጠበቅ የቻሉትን ሁሉ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው አሳስባለች። “ይህ የአሜሪካ ሙስሊም ወጣቶች ማዕከል የወጣቶቻችን ቦታ ነው እና እሱን ለመጠበቅ ቆርጠን ተነስተናል” ብላለች። ” በህዝቡ እንደመመረጣችን በእነዚህ ቦታዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እና እነዚህ የጥላቻ ወንጀሎች በአግባቡ ሪፖርት እንዲደረጉ ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።” ስትል አክላለች።
ከተመረጡት ባለስልጣናት እና የማህበረሰብ አባላት ድጋፍ ጋር የአንድነት ቀን የሲያትል ወጣቶች ተስፋ፣ ራዕይ እና አንድነትን አንጸባርቋል። ዝግጅቱ የተሰናዳው በአሜሪካ ሙስሊም ወጣቶች ማእከል የቅርጫት ኳስ ጂምናዚየም ሲሆን ይህም ለብዙ ወጣቶች እንደቤታቸው እንዲሰማቸው አድርጓል። የ ዋሽንግተን አስተዳዳሪው ጄይ “ከአንዳንድ ታላላቅ አሜሪካዊ ሙስሊም ወጣቶች ጋር ጥቂት ቅርጫት ኳሶችን ለመምታት ተመልሼ እንደምመጣ ተስፋ አደርጋለሁ።” ብለዋል።