ትውልደ ኢትዮጲያዊትዋ የ ኔዘርላንድ ዜጋ የሆነችው ሲፈን ሀሰን በድጋሚ በ 2020 የ ቶኪዮ ኦሎምፒክ ባሳየችው ድንቅ እንቅስቃሴ የአለምን ህዝብ አስደንቃለች። በተሳተፈችባቸው ሶስት የሩጫ መስኮች ላይ በስኬት ያጠናቀቀችው ሲፈን በ አምስት እና አስር ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት እንዲሁም በ አንድ ሺህ አምስት መቶ ሜትር ደግሞ የነሐስ ሜዳልያ በማሸነፍ በኦሎምፒክ ታሪክ 3 ሜዳልያ ያሸነፈች የጀመርያዋ አትሌት ሆናለች። ሲፈን ካሸነፈች በኋላ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ “ለአለፉት አራት አመታት ይህንን በማሰብ ስዘጋጅ ከርምያለው። አሁን አርፍያለው!” ብላለች።
ሲፈን የአለምን ህዝብ ባልታሰበ ብቃትዋ ከማስገረምዋ በተጨማሪ አብረዋት ሮጠው የተከተሏት ከዚህም በተሻለ እንደምትመጣ አውቀዋል። የ 28 አመትዋ ሲፈን አለም አቀፍ ተፅዕኖን ማግኘት የቻለችው የእድሜዋን አስራዎች ካገባደደች በኋላ በኒጅሜጋን አለም አቀፍ የአትሌትክስ ውድድር እና በ ጎልደን ስፓይክ ኦስትረቪ የ 1500 ሜትር ውድድርን ካሸነፈች በኋላ ነበር።
በ 2013 በስዊዘርላንድ በተደረገው የዳይመንድ ሊግ የ 1500 ሜትር ተፎካካሪ የነበረችው ሲፈን በ ስቶኮልም በተደረገው የ 3000 ሺህ ሜትር ውድድር ደግሞ 3ተኛ በመሆን አጠናቃለች። በዚህ ወቅት በአለም አራተኛዋ ፈጣን ሯጭ የነበረች ሲሆን በ 2013 መባቻ ኔዘርላንድን ለመወከል የሚያስችል የደች ዜግነት አጊንታለች።
በ 2013 የስዊዘርላንድ ዜጋ ከሆነች በኋላ የ አውሮፓ ሀገር አቋራጭ ሩጫን በመሳተፍ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳልያ ከማሸነፍዋ ባሻገር የቡድን አጋሮችዋ በአጠቃላይ ውጤት የ ሶስተኛነት ደረጃን እንዲቀዳጁም አድርጋለች። ሲፈን በታሪክ ላይ ስሟን ለማስፈር ግዜ አልወሰደባትም። ዜግነቷን ባገኘች በአንድ አመትዋ በ 2014 በርሚንግሀም የቤት ውስጥ ሩጫ የ1500 ሜትር ውድድር በ 4:05:34 ደቂቃዎች በመግባት የደች ክብረ ወሰንን ሰብራለች።
የሲፈን ሀሰን ስኬት ያለምንም ጋሬጣ እና ችግር የመጣ አይደለም። በ 2019 አሰልጣኝ አልቤርቶ ሳላንዛር በአሜሪካ የፀረ ዶፒንግ ኤጀንሲ የታገደ ሲሆን የቀረበበት ክስ የ ቴሥቴስትሮን እና ከተፈቀደው በላይ ኤል ካራንቲን የተባለ አነቃቂ እፅ በመያዝ የዶፒንግ ህግጋትን ተላልፏል የሚል ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሲፈን ስም አብሮ በመነሳቱ በግዜው የነበራት ስኬት ላይም አሉታዊ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል። በግዜው ሲፈን ሀስን በዶሆ በተደረገው ቻምፕዮን ሺፕ በ 1500 እና በ 10000 ሜትር በአንድ ግዜ ወርቅ በማምጣት የመጀመርያዋ ሰው ሆና ነበር።
የማይገልህ ያጠነክርሀል እንዲሉ ሲፈን ከዚህ ክስተት በኋላ ይበልጥ ጠንክራ በመምጣት ባልተጠበቀ ሁኔታ በ ዶሆ እና በቶኪዮ ታሪክ ሰርታለቻ። ቀጣይ 2024 በፓሪስ በሚደረገው ኦሎምፒክ ላይ እድሜዋ 31 ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ ታሪኮችን የምትሰራበት እድል እንዳለ ይጠበቃል።