የ ህውሓት ወታደሮች ቀስ በቀስ ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እየቀረቡ መምጣታቸውን ተከትሎ በ ህዳር 2/2021 የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። በዚህ የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሃገሪቱ የመግባት እቅዳቸውን እንዲሰርዙ ከማስገደዱ ባሻገር በዋና ከተማዋ ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች በከተማው ታጥረው ለመቆየት ተገደዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰዓት እላፊ ገደቦችን መጣሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ እና በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ ብሔራዊ የደህንነት ስጋቱ መሻሻል በማሳየቱ ለ ስድስት ወር የረቀቀው አዋጅ ግዜው ከመገባደዱ አስቀድሞ ተነስቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ሀሳብ አንድ ወር አስቀድሞ በፓርላማ ቀርቦ ነበር። መንግስትም የህወሀት መሪዎችን ጨምሮ ለብሔራዊ ምክክር መድረኩ ስኬት ሲባል በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር ነጻ አድርጓል። ፓርላማው ይህንን ጥያቄ በ የካቲት 15 ባደረገው ስብሰባ የአስቸኳይ ግዜውን በማንሳት መልሷል። ይህ ለዜጎች አንፃራዊ ሰላምን ከመስጠቱ ባሻገር ሀገሪቱ የገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት መቋጫ ይሆን? የሚል የተስፋ ጫላንጭልን ጭሯል።
በፌዴራል መንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎች በ በርካታ እውቅና እና ይሁንታን ተችሮታል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መነሳቱን አስመልክቶ “ወሳኝ እርምጃ” ሲል አፋጣኝ ምላሽ ሰጥቷል። የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በመግለጫው “ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተወሰደ ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ እናስባለን።” ብሏል።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅት ያለምንም ክስ የታሰሩ እና በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያሉ ሁሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።
የፌደራል መንግስት ጦርነቱን ለመቋጨት አስፈላጊውን እርምጃ ቢወስድም ህወሓት በብሔራዊ መግባባቱ ላይ ይሳተፋል? መንግስትስ ከህወሓት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነው? የሚለው ጥያቄ ከመሆን አልተወገደም። በጦርነቱ መንግስት ህወሀትን ከሽብርተኛ ድርጅቶች መሀል የፈረጀው ሲሆን በብሔራዊ ውይይቱ ላይ አሸባሪዎች ተሳታፊ እንደማይሆኑ አስታውቋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መንግስት ህወሀትን ከአሸባሪ ድርጅቶች ተርታ እንዲያወጣ ጫና እየተደረገ እንደሆነ ገልፀው “የታቀደው ብሔራዊ ውይይት ድርድር አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥትም ሕወሓትን ጨምሮ በአሸባሪነት ከተፈረጀ ቡድን ጋር የመደራደር አጀንዳ የለውም።” ሲሉ አፅንኦት ሰተው ተናግረዋል።
ብሔራዊ ውይይቱ ህውሓትን ካላካተተ በኢትዮጲያ እውን ጦርነቱ መቋጫ ያገኛል? የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው። የፌደራል መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን እየፈታ ቢሆንም ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ውጪ ያሉት ሙሉ በሙሉ ነፃ ናቸው ማለት ግን ይከብዳል። በድጋሚ ተከሰው ፍርድ ቤቱ እጣ ፈንታቸውን የሚወስን ይሆናል።
በ 35ኛው የአፍሪካ ህብረት ምክር ቤት ስብሰባ የተመድ ዋና ፀሀፊ ተወካይ ሆና የተገኘችው አሚና መሀመድ “ከብሔራዊ ውይይቱ ጋር ተያይዞ እንዲሁም ወደ ሰላም የሚደረገውን ጉዞ ተከትሎ ንግግሮች እና ውይይቶች አሉ።” ብላለች።
አሚና ኢትዮጵያን በጎበኘችበት ጊዜ የትግራይ፣ የአማራ፣ የሶማሌ እና የአፋር ክልሎችን ማየት ችላለች። የነዚህን ክልሎች ሰብአዊ ቀውሶች ከተመለከተች በኋላ የሰላም ተስፋ ሰንቃ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላማዊ ውይይት እና ድርድር ጠርታለች። ነገር ግን ሰላማዊ ውይይቱ ህወሓትን የሚጨምር ካልሆነ የሰላም ሽግግሩ ምን ያህል ፍሬያማ ይሆናል የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።
አሚና “አሁን ላይ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው ያነሰ ግጭት ነው ያለው!” ብላለች። ምናልባትም ከእስር የተፈቱ እስረኞች እጣ ፈንታ ያልታወቀ ከመሆኑም ባሻገር የተወሰኑ ግጭቶች አሁንም አሉ። የኢትዮጵያ ዜጎች ይህ እልባት አጊንቶ ላለፉት ሁለት አመታት ተሳፋ ሲያደርጉ የነበረው ሰላም ተመልሶ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው የሚመለሱበትን ጊዜ እየጠበቁ ነው።